“ይቅር መባባሉ ይጠቅማል ብለን ስላመንበት ይቅር ብለናል”

Date:

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደረገውን የጥላቻ ንግግር ጉባኤው እንዲመለከተውና ችግሩን መርምሮ ሁሉንም አካላት የሚጋብዝ የሰላም ጥሪ ለማስተላለፍ ከቦርዱ አባላት ጋር ቀጠሮ ቢይዝም ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውጭ ሌሎች አብያተ እምነት ተወካዮች ሳይገኙ መቅረታቸው የሚታወቅ ነው። ኾኖም ታኅሣሥ 25 ቀን 2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በጉዳዩ ላይ በመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ውይይት በማካሄድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ ጠይቀዋል።

ውይይቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት የስድስቱም አብያተ እምነት የበላይ ጠባቂ አባቶች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

በዕለቱም የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ “የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲከፋት ሁላችንም ይከፋናል” ያሉ ሲሆን ይቅር ተባባሉ ብለን ስንሰብክ እኛ ይቅር ካልተባባልን ትርጉም የለውምና ይቅር በሉን ሰይጣን ይፈር አንድነታችንን እናጠንክር ብለዋል። ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው “በተደረገልን አቀባበል በጣም ደስ ብሎናል በሀገራችን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እናት ናትና በአዘነ ልብ ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለዋል። በራሳችን መሀል ያለውን አለመግባባት ራሳችን እንፈታለን ወደፊት ወደተሻለ ሰላም እና አንድነት ለመሄድ ተስማምተናል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ተወካይ ፓስተር ጻድቁ አብዶ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ ለመጠየቅ መተናል” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም በሃይማኖት መካከል ለሚፈጠሩ ችግሮች ከፍተኛ ውይይት አድርገን እንፈታለን፤ የሌላውን ሃይማኖት በማንቋሸሽ የሚገኝ ጥቅም የለም በዚህ በሰፊው እንመክራለንም ብለዋል። የኢትዮጵያ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ በበኩላቸው ”እናት ቤተ ክርስቲያን በማዘኗ ደንግጠና”ል ያሉ ሲሆን ”የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እናታችን ነች ይቅርታ ጠይቀናል ይቅርም ብላናለች” ሲሉ ተናግረዋል። ”በፍቅር ተቀብለውናል ይቅርታ ጠይቀናል ማበር ወይም ማደም አመፅ ነው። በዚህም የተፈጠረውን ስህተት ለማረም እዚህ ተገኝተናል።” ያሉት ደግሞ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ተወካይ ናቸው። ክፍተቱን በጋራ ለመፍታት ተስማምተናል ይቅርታ ስለጠይቅን ይቅርም ስላሉን ደስ ብሎናልም ብለዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በአስተላለፉት መልእክት ”እኛ ያሳዘኑንን ይቅር ብንል እግዚአብሔር ደሞ ይቅር ይለናል ብለን እንደ ቃሉ እናምናለን” ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ”ይቅር መባባሉ ለሀገር፣ ለወገን፣ ለሃይማኖት ይጠቅማል ብለን ስላመንበት ይቅር ብለናል። ሁላችንም ተሰብስበን ይቅርታ መደራረጉ መልካም ነው ወደፊት መሰል ነገር እንዳይፈጠር ይረዳል” ብለዋል። ቅዱስነታቸው ”ሃይማኖት እንደ ዐይን ብሌን የምንጠብቀው ነው፤ የተነገረውን ነገር ለማስታገስ ነው ይቅርታውን የተቀበልነው፤ ይቅር መባባሉንም እግዚአብሔር ይወደዋል” ብለዋል። ቤተ ክርስቲያን ቅር ብሏታል ይቅርታ እንጠይቅ ብላችሁ ስለመጣችሁ እናመሰግናለን ሲሉ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...