የዛሬው ባለታሪካችን የተወለዱት በኦጋዴን አካባቢ ካልካዩ በተባለ ሥፍራ ሲሆን ዓመቱም 1871 ዓ.ም ነው፡፡ በልጅነታቸው የተለያዩ ሀይማኖታዊ ትምህርቶችን ባህላዊ ሥርዓቶችን እየተማሩ ያደጉት እኝህ ሰው የአስተዳደር ሰው ለመሆን በነበራቸው ፍላጎት የመሪነት ክህሎታቸውን ሊያሳኩ የሚችሉ የተለያዩ ጥረቶችን እየሞከሩና ከአካባቢው የጎሳ መሪዎች አሰራርና ተሞክሮን እየቀሰሙ ማደጋቸው ይነገራል፡፡ ለአካለ መጠን ሲደርሱም በአካባቢ አስተዳደር ስራ በመሰማራት አገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን በቅድሚያ በባላባትነት ማዕረግ በመቀጠልም የሱልጣን ዓሊ የሱፍ እንደረሴ ሆነው በናኢባነት እንደዚሑም የኤል-ቡር ገዢ በመሆን ለ23 ዓመታት አገራቸውን በፍጹም ቅንነት አገልግለዋል፡፡
የታሪክ ጠላታችን ፋሺስት ኢጣልያ የዓድዋ ሽንፈቱዋን ለመበቀል ሴራ መጠንሰሱዋን አሀዱ ያለችው በወልወሉ ግጭት ነበር፡፡ የወልወል ግጭት መሠረቱ እንዲህ ነው፡፡
የእንግሊዝና የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊያ በኩል ባለው የግዛታቸው ወሰን በደንብ ለመከለል ስምምነት አድርገው ስለነበር ቀን ተቆርጦ ወደስራ ሲገባ ሥራውን እንዲያከናውኑ ከእንግሊዝ ኮሎኔል ክሊፎርድ ከኢትዮጵያ ወገን ደግሞ ፊታውራሪ ተሠማ ባንቴ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት የወሰን ክልሉን ለማጥናት በተንቀሳቀሱበት ወቅት ካፒቴን ሺማትሩ የተባለ የኢጣልያ ተወላጅ ቀደም ሲል ከደረሰበት የወሰን ስምምነት መቶ ኪሎ ሜትር የሚያህል አልፎ እንደጠብ አጫሪነት መተላለፊያ ከለከለ፡፡ በዚህ ነገር ግራ የተጋቡት የኢትዮጵያ ተወካዮች በሰውየው አድራጎት ላይ ማብራሪያ ለመስማት እንኩዋን ባላስቻለ ፍጥነት ጦሩን አዝምቶ በአየርና በምድር ጦርነት በመክፈት ያለተዘጋጁትን የኛን ወገኖች አጠቃቸው፡፡ በዚህ ጦርነት ፊት አውራሪ አለማየሁን ጨምሮ ቁጥራቸው 107 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በክብር ሲወደቁ 75 ያላነሱ የፋሽስት ወታደሮች ሞቱ፡፡
መጋቢት 5 ቀን 1977 ዓ.ም. በወጣው የ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ከተፃፈው ለመረዳት እንደሚቻለው ከ1927 ዓ.ም. አንስቶ ጣሊያን በሶማሊያ በኩል የትንኮሳ ጦርነት ስታደርግ የኢትዮጵያ ድንበር እንዳይጣስ ይከላከሉ ከነበሩት አንዱ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ናቸው፡፡ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል በኦጋዴን ድንበር የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ለእርቅ በተቀመጡ ጊዜ ተወካዩ “በጣሊያን ላይ በደል የፈፀመው ዑመር ሰመተር እጁን ተይዞ ይሰጠኝ” ሲል ጠይቆ ነበር፡፡ የጣሊያን ጥያቄ ምን እንደነበር በተነገራቸው ጊዜ “ከአፈር የሚደባልቅ ቤልጅግና ጐራዴ ይዤ ነው እጄን የማሳየው፤ ጫት ተሸክሜ የምሄድ አልምሰለው” ሲሉ መልስ መስጠታቸው ተመዝግቧል።
ደጃዝማች ዑመር ሰመተር የአጣልያ ጦር በወልወል የጫረው እሳት በሰሜን ተያይዞ በነበረበት በዛ ቀውጢ ቀን አገር በጣልያን እንዳትወረር በዱር በገደሉ ሲጠባበቁ በነበረበት ወቅት በምሥራቁ ኢትዮጵያ ክፍል ከደጃች አፈወርቅ ወልደሰማያት ጋር በመሆን ዑመር ሰመትር የትግሉን ጎራ ተቀላቀሉ፡፡ በዚሕም ወቅት ከአቻ ወንድሞቹ ጋር በተለያዩ የጦር ዐውደ ግንባሮች የተሰለፈው የሶማሌ ጦር ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጥቶ የእግር እሳት ሲሆንበት በተለይም ደግሞ በዑመር ሰመተር የሚመራው ጦር ጎርበሌ ላይ መሽጎ እየወረወረ የጠላት ጦርን መድረሻ አሳጣው፡፡ በመሪው በኡመር ሰመተር ኢትዮጵያውያን በድል ጎዳና ተራመዱ፡፡ አይቀጡ ቅጣት የተቀጣው የጠላት ጦር ሊመሽበት እንደሆነ ተረዳና ከሱው ብሶ ስሞታ ለዓለም መንግስት አሰማ፡፡ በዚህ ስሞታው ካሳ እንዲከፈለው ብቻ አልጠየቀም ፤ ጀግናው ዑመር ሰመተር እንዲሰጠው ጭምር እንጂ፡፡ በተለያዩ የጦር አውደ ግንባሮች ድልን መጎናጸፍ የጀመረው የዑመር ጦር ኤል ቡር ላይ ፋሺስት ቦታውን በስድስት ባታሊዮን ጦር ተከበበ፡፡ እውነታው የገባቸው የጦር አበጋዙ ለጊዜውም ቢሆን ማፈግፈጉን መረጡ፡፡ ፋሽስት ድል ያገኘ መሰለው፡፡ ይሁንና ለ5 ወራት ያህል ጦራቸውን በማደራጀት የቆዩት ዑመር በ1930 ዓ.ም ሌሊት በጠላት ጦር ላይ ያልታሰበ አደጋ ጣሉ፡፡ ያንን የተፈራ ባለ ብዙ ባታልዮን ጦር ከጥቅም ውጭ አደረጉት፡፡ በድል እየዘመሩ ለሌላ ጥቃት ሽላቦ ላይ ሰፈሩ፡፡ አሁንም ፋሺስት ሽላቦ ድረስ እየመጣ አላስቀምጥ አላቸው፡፡ እንደገና ገጥመው ድል አደረጉት፡፡ በቆራሄም ጠላት አፈረ፡፡ ከጠላት ምሽግ የጨበጣ ውጊያ በማካሄድ ታላቅ ጀብዱ ፈጸሙ፡፡
የጠላት ጦር ኃይሉ እየከበደ ሲመጣ በጉርለጉቤው ጦርነት ዑመር በጠላት ጥይቶች ተመቱ፡፡ ደጃች ዑመር ሰውነታቸው በስድስት ጥይቶች በመቁሰሉ በጦርነት ለመሳተፍ ከማችሉበት ደረጃ ደረሱ፡፡ በዚሁ ምክንያት ለህክምና በቅድሚያ ሀርጌሳ ከዛም በኬንያ በኩል ተጉዘው ወደ ሎንደን ተላኩ፡፡ እስከጦርነቱ ማብቂያ በሎንዶን የቆዩት ዑመር ሰመተር ነጻነት ሲመለስ ባንዲራ ሲሰቀል አርበኛው ሁሉ እየፈኮረና እያቅራራ ግዳጅ ሲጥል የድል አጥቢ አርበኛውም ለጀግንነቱ ምስክር ሲገዛ ፊታውራሪ ዑመር (በሁዋላ ደጅ አዝማች) በኦጋዴን ከጦርነቱ የተረፉትን አርበኞች አክብረው የሚገባቸውን ሸለሙዋቸው!!!
ታላቁ ጀግናችን ዑመር ሰመተር የተጣባቸው የጠላት ጥይት ጤና እየነሳቸው ቁስሉም እየመረቀዘ ስላስቸገራቸው በሐረር ከተማ ሀኪሞች ባሉበት ቦታ ሁሉ እየተዘዋወሩ ቢታከሙም ለመዳን ግን ሳይችሉ ቀረ በተወለዱ በ61 ዓመታቸው መጋቢት 10 ቀን 1936 ዓ.ም ከዚሕ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
ሐረር ከተማ በሚገኘው በአብደል መካነ መቃብር መኳንንቶች አስከትለው ክርስቲያንና እና እስላሙ በነቂስ ወጥቶ ለጀግና በሚሆን በሙሉ ወታደራዊ ክብር ተሸኙ!!!
በዚህ የቀብር ሥነ ሥርዓት አብዶ ሀይድ የተባሉ የትግል ጓዳቸው ይህንን አንጀት የሚበላ ቅኔ ተቀኙላቸው፡-
ተገዳይ እወልወል እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ አፍዱግ ላይ እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ ቆራሄ እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ ሀነሌ እጠረፉ ላይ፤
የመትረየሱ ሼክ የለበን መምህር፤
ሞት ጠራህ አንተንም ዑመር ስመጥር!!!
ለእኚህ ታላቅ የሀገር አርበኛም ከአንድ ዓመት በፊት መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በሥማቸው የሚጠራ ትምህርት ቤት ዳግም ተሠይሟል። በጀግናው ሥም እንዲጠራ የተሠየው ትምህርት ቤት በከተማው ኮልፌ አጠና ተራ እፎይታ የገበያ ማዕከል አካባቢ ይገኝ የነበረው እፎይታ ት/ቤት ነው። ትምህርት ቤቱ በአዲሱ ሥያሜው ‹‹ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ስም አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት›› በሚል እንዲጠራ በተወሰነበት ሥነ ሥርዐት ላይ የደጃዝማች ዑመር ሰመተር የልጅ ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ተገኝተውም ነበር። በአዲስ አበባ ከተማ በደጃዝማች ዑመር ሰመተር ሥያሜ ይጠራ የነበረው በመርካቶ አንዋር መስጂድ ጀርባ ይገኝ የነበረው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በልማት ምክንያት መፍረሱ ይታወቃል።
ክብር ለነጻነት ላበቁን አባቶቻችን!!
