
ድርቅ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በተለያየ ዓለም ላይ የሚከሰት ተፈጥሯዊ አደጋ ነው፡፡ የሰው ልጅ ይህን ተፈጥሯዊ አደጋ ማስቀረት ባይችልም መጋፈጥና መቋቋም የሚችልበት ልዕልና ግን አለው፡፡ እንደኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ደግሞ ይህ ተፈጥሯዊ አደጋ በየጊዜው የሚያጠቃቸው ግንባር ቀደም ሀገራት ናቸው፡፡ የድርቁ በየጊዜው መመላለስ ዓይነተኛ ምክንያቱ ሀገሪቱ በዘርፉ የምትከተለው ጠማማ ፖሊሲ መኾኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ መንግሥታቸው በዘርፉ የሚከተለውን ፖሊሲ ላለመንቀፍ ሲሉ “ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ርሃብ ግን የሥንፍናችን ውጤት ነው” ሲሉ በሰሞነኛው መግለጫቸው አስቀምጠውታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መግለጫቸው ሀገራችን ኢትዮጵያን ድርቅ በየአሥር ዓመቱ እየተመላለሰ እንደሚያጠቃት እና በታሪካችን በዚህ ልክ የፈተነን ጠላት አለመኖሩን ያነሳሉ። አያይዘውም በዚህ እየተመላለሰ በሚከሰተው ድርቅ የበርካታ ዜጎች ሕይወት እንደሚቀጠፍ፣ ብዙ ሕጻናት በምግብ እጥረት ሳቢያ ለመቀንጨር እንደሚገደዱ፣ ወጣቶችን ለስደት እንደሚዳረጉ፣ አረጋውያንን ለጉስቁልና እንደሚጋለጡ፣ የቀንድና ጋማ ከብቶቻችንን ለእልቂት እንደሚዳረጉ ያትታሉ። አክለውም ሉዓላዊነታችን እንዳይደፈር የምናድርጋቸው ተጋድሎዎች በርሃብና ቸነፈር ላይ አለመደገማቸው ይህን ያህል ዋጋ ሊያስከፍለን እንደቻለ ይጠቅሳሉ። አስከትለውም በምግብ ራሳችንን ባለመቻላችን ምክንያት ብሔራዊ ሕልውናችን ስጋት የተሞላበት ሲኾን የእለት ጉርሳችንን አሸንፈን እስካልተገኘን ድረስ በየትኛውም ዘርፍ የምናስመዘግበው ስኬት ትርጉሙ የደበዘዘ እንደኾነና የግብርና ምርቶች ላይ የምናሳየው ድክመት በኢኮኖሚው ብቻ ሳይኾን በማኅበራዊም፣ በፖለቲካውም፣ በዲፕሎማሲና በሌሎች ዘርፎችም ላይ ተጽእኖ እንዳለው ያብራራሉ።
ከዚህ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ አንድ ነገር መታዘብ ይቻላል፡፡ ይኸውም የሁሉ ነገር መነሻ ችግራችን ድርቅና ረሀብ መኾኑን ግንዛቤ መውሰድ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደእርሳቸው ገለጻ ሕልውናችን ለአደጋ የተጋለጠውና ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ውድቀታችን ምንጩ ድርቅና ረሀብ ነው፡፡ ይህ አገላለጽ ከእውነት የተጣላ ነው፡፡ ምክንያቱም የውድቀታችን ሁሉ ምንጭ ፖለቲካዊ አመራር እንጅ ድርቅና ረሀብ አይደለም፡፡ የተሳለጠ ፖለቲካ ያለባቸው ሀገሮች ለድርቅ ተጋልጠው አላየንም፡፡ አንጻራዊ ዲሞክራሲ የሚታይባቸው ሀገሮችም ዜጎቻቸው የድርቅ ሰለባ ሲኾኑ አላስተዋልንም፡፡ ሁልግዜ በድርቅ ሲጠቁ የምናያቸው የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ናቸው፡፡ እነርሱም የረጋ ፖለቲካዊ መዋቅር የሌላቸው እና በየጊዜው በጎሳና በልዩ ልዩ አመክንዮ የሚናቆሩ ሀገሮች ናቸው፡፡ ይጠቀሱ ቢባል እንኳ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በተወላጆቿ “የበረሀ ገነት” የምትሰኘው ጂቡቲና የ30 ዓመት ወጣት የኾነችው ሀገረ ኤርትራ የዚህ ችግር ሰለባ አይደሉም፡፡ በርሀብ ምሳሌነት የተቀመጡት ሀገራት ግን በየገዜው በጎሳ ፖለቲካ የሚታመሱ ናቸው፡፡
ስለዚህ በሀገራችን ላይ ሥምረት ያለው ፖለቲካዊ ሥርዓት ከተገነባና ሀገሩን የሚወድ ዜጋ በሀገሪቱ የሥልጣን መንበር ላይ ከተቀመጠ ችጋርና ረሃብ ታሪክ ኾነው የማይቀሩበት አንዳች ምክንያት የለም፡፡ ሙስናና ዘር የቆፈነነው ሥርዓት በሀገራችን ላይ ተንሠራፍቶ ባለበት ሁኔታ ግን “ረሀቡ የመጣው በስንፍናችን ነው” ብሎ ማውጋት ለችግሩ መፍትሔ አይኾነውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚያ ይልቅ ዛሬ ላይ በእጃቸው የሚገኘውን ሥልጣን በአግባቡ ተጠቅመው ሙሰኞችንና ዘረኞችን ጥግ አስይዘው ችጋር ቀራፊ ፖሊሲን ነድፈው ቢንቀሳቀሱ ይበልጥኑ ለሀገሪቱ ይጠቅም ነበር፡፡ ሀገር በመግለጫ የምትበለጽግ ይመስል በየሳምንት መግለጫ ማውጣት የአስመሳይነትና የቀላማጅነት አባዜ እንጅ የውጤታማነት መለኪያ አይደለም፡፡ ለተራበ ሕዝብ ከመግለጫ ይልቅ ሕይወቱን የሚያቆይለት ዳቦ ነው፡፡ ዳቦ ለመሥራት ደግሞ ፖለቲካዊ መደላድሉን ማመቻመች ያስፈልጋል፡፡ በየትኛውም ዘርፍ ብቁ አመራር በሌለበት ሀገር ላይ ከቸነፈር የጸዳ ዜጋን መምራት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የብልጽግና ካድሬዎችም የዘር ኮታ ለሟሟላት የተፈናጠጡበትን ሥልጣን ዜጋን ለማገልገል ሊያውሉት ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ የዘር ሴራን ሲፈትሉ በመዋል ብቻ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡
በሌላ በኩል በቅርቡ የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ድርቅ ሀገሪቱ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ሰላባ ለመኾኗ ማሳያ መኾኑን አስታውቋል። የኤጀንሲው የአየር ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ጫሊ ደበሌ በኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ ሶማሌ፣ በቦረና፣ በጉጂ እና ባሌ ቆላማ አካባቢዎች የተፈጠረው ድርቅ ከፓስፊክ ውቅያኖስ የላይኛው አካል የሚነሳው ”ላሊና” ተብሎ የሚጠራው አየር ከመደበኛ በላይ መቀዝቀዝ ያስከተለው የዝናብ እጥረት መኾኑን ገልጸዋል። ይህንን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጦችን እና በዚያ ሳቢያ የሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚተነብየው ብሔራዊ የሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ ቢያደርግም ትንበያው የአጫጭር እንጂ የረጅም ወቅቶች አይደሉም ብለዋል። ከዚህ አኳያ ኤጀንሲው ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት የነበረበት ቢኾንም ያን ማድረግ አልቻለም፡፡ ለምን የሚል ጥያቄ እንዳይነሳም የአጫጭር እንጂ የረጅም ወቅቶችን ሁኔታ እንደማይተነብይ እዚሁ አስቀምጧል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍ ሲል ከተነሳው የአመራር ብቃት ችግር ጋር የሚያያዝ ይመስላል፡፡ የትንበያ ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር የማስገባት ኃላፊነት የተቋሙ መኾኑ አያጠያይቅም፡፡
በሌላ ወገን በድርቁ ለተጠቁ 57 ወረዳዎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እየተሠራ መኾኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር እንድርያስ ጌታ ገልጸዋል፡፡ ድርቁ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመቅረፍ በሦስት ፈርጆች የመፍትሔ ዕርምጃ እየተወሰደ መኾኑን የገለጹት ዶ/ር እንድርያስ፤ በድርቁ ለተጠቁ ወገኖች በአንደኛ ደረጃ አስቸኳይ የነፍስ አድን ሥራ ማለትም ለተጎጂዎች የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የውሃና የእንስሳት መኖ አቅርቦት፤ በሁለተኛ ደረጃ የአጭር ጊዜ መልሶ ማቋቋም ማለትም አዳዲስ የውኃ ጉድጓድ መቆፈርና የተቆፈሩ ውሃ ጉድጓዶች ጥገና ማድረግ፣ መኖ ማምረትና የመኖ መጋዘን ማዘጋጀት፣ የውኃ ፓምፖችን በመጠቀም ውኃ ካለባቸው አካባቢዎች ስቦ ለተጎጂዎች ተደራሽ ማድረግ ሲኾን በሦስተኛ ደረጃ ዘላቂ ልማት ማምጣት ማለትም እነዚህ አካባቢዎች የተፈጥሮ አደጋዎችን እንዲቋቋሙ የመስኖ ልማትን ማስፋፋት፣ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ማከናወን፣ አማራጭ የገቢ ምንጮችን ማሳደግና መሰል ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡
በተያያዘ በሶማሌ ክልልም እንዲሁ በድርቁ ምክንያት በሰዎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የክልሉ መንግሥት እያከናወነ ያለው የአፋጣኝ ምላሽ ሥራዎች ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል። የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሀመድም በሶማሌ ክልል በተከሰተው ድርቀ ሳቢያ በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በተለያዩ አካባቢዎች የእስሳት መኖ የማልማት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ወቅታዊ ድጋፍ ማድረግ ብቻውን የተከሰተውን ችግር በዘላቂነት ሊፈታው አይችልም፡፡ መንግሥት በድርቅ ለተጎዱት አካባቢዎች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እንደቦረናና ጉጂ ባሉ አካባቢዎች አሸባሪው ሸኔ የሚንቀሳቀስባቸው ቦዎች በመኾናቸው መንግሥት በአንክሮ ሊሠራበት ይገባል፡፡ አሁን ላይ ድርቅ በተከሰተባቸው በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጋርጠዋል፡፡ በቦረና እና ምስራቅ ባሌ ዞኖች ባሉ 14 ወረዳዎች ብቻ 61 ትምህርት ቤቶች በድርቅ ምክንያት ተዘግተዋል። በምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፣ በቦረና፣ በምዕራብ ጉጂ፣ በምዕራብ አርሲ እና ባሌ ዞኖች በሚገኙ 70 ወረዳዎች ውስጥ በ605 ቀበሌዎች 2.8 ሚሊዮን ሕዝብ የመጠጥ ውኃ ይፈልጋል። 257 ሺ እንስሳት አቅም አንሷቸዋል። በቦረና እና ምስራቅ ባሌ ዞኖች አካባቢዎች ከ 3.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ይሻሉ። በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል 915 ት/ቤቶች ከሥራቸው ተስተጓጉለዋል። ከነዚህ 316ቱ ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል። በ83 ወረዳዎች 3.1 ሚሊዮን ሕዝብ ለውኃ እጥረት ተጋልጧል። 2.4 ሚሊዮን ሕዝብ ለምግብ እጥት ተጋልጧል። ከእነዚህ እና አጠቃላይ 3 ሚሊዮን 360 ሺህ ሕዝብ የምግብ ድጋፍ እንደሚሻም ተናግሯል። ከሐምሌ እስከ የካቲት ባለው የድርቅ ጊዜ 864 ሺህ 43 እንስሳት መሞተዋል። 58 ሺህ 305 ሰዎች በድርቁ ተጠቅተዋል። ከዚህ አኳያ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሚና መወጣት ይኖርበታል፡፡ ዜጎቹን ከቸነፈር መታደግ መንግሥታዊ ግዴታው መኾኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህን ችግር በመግለጫ ማስቆም አይቻልም፡፡