ድንበር ተሻጋሪ ሴት ነጋዴዎች በአፍሪካ!

Date:

ፓን አፍሪካን ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ከኢንዱስትሪ ሼርድ ቫሊው አፍሪካ ጋር በጋራ በመሆን በመጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም “International Livestock Research Institute (ILRI)” ግቢ ውስጥ ‹‹የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ለንግድ ማህበረሰብ የሚሰጠው ጠቀሜታ›› በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር።

በዚህ የውይይት መድረክ የፓን አፍሪካን ቻምበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክቡር ገናን ጨምሮ፣ የሼርድ ቫሊዩ አፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ቩዮ ሉትሰካ፣ የቻድ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ፕሬዝዳንት ዓሊ ሀጂ ማሕመት ሰኢድ፣ የጋና ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ኤንድ ኢንዱስትሪ ፕሬዝዳንት ክሌመንት ኦሴ-አሞዋኮ፣ የሳፋሪኮም ኮርፖሬት ጉዳዮች ዋና ኦፊሰር ስቴፈን ኪፕቹምባ እና የተለያዩ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን በተለያዩ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል። በውይይት መድረኩ አንደኛው የመወያያ አጀንዳ የነበረው ‹‹ድንበር ተሻጋሪ ሴት ነጋዴዎች›› መደበኛ ባልኾነ አህጉራዊ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸውን ድርሻና ተሳትፎ የሚመለከት ነበር፡፡ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-  

መግቢያ

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ከኾነ፣ ሴቶች በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ የንግድ ለውውጥ ውስጥ 43 ከመቶ የሚኾነውን የአህጉሪቱ ገቢ እንደሚያበረክቱ ይገመታል፣ ዳሩ ግን አሁናዊ ትክክለኛ የንግድ አበርክቷቸው 10 ከመቶውን ብቻ የያዘ ነው።

እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ከኾነ ደግሞ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ አነስተኛ የንግዱ ማኅበረሰብ ውስጥ ሴቶች 90 በመቶ የሚኾነውን ይሸፍናሉ።

አሁንም በተመድ መረጃ መሠረት፣ በአፍሪካ 70 በመቶ የሚኾነውን መደበኛ ያልሆነ ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ሥራ ሴቶች እንደሚያከናውኑት ይገመታል።

በየቀጣናው ምን መልክ አለው?

የአፍሪካ ሴቶች አግሪቢዝነስ ኔትወርክ (AWAN Africa) ከተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ጋር ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ተግባራት መሣለጥ በአጋርነት ቆሟል፡፡

በደቡብ አፍሪካ፣ ሴት ነጋዴዎች ከሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ ሲኾን 70 በመቶ የሚኾነው ንግዳቸው ደግሞ ጥሬ ዕቃዎችን እና በከፊል የተቀነባበሩ ምርቶችን የያዘ ነው።

በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ደግሞ ሴት ነጋዴዎች ከ60 በመቶ በላይ መደበኛ ባልኾነ የድንበር ተሻጋሪ ንግድ ውስጥ ተሰማርተው፣ ከ40-60 በመቶ የሚኾነውን የሀገር ውስጥ ምርት ያመርታሉ።

በምሥራቅ አፍሪካ ሴት ነጋዴዎች በዚሁ መደበኛ ባልኾነ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ተሳትፈው 40 ከመቶ በሚኾነው የጋራ ገበያ ውስጥ ይገኛሉ።

መደበኛ ባልሆነ ንግድ ውስጥ ያሉ ሴቶች የቤተሰብ አባሎቻቸውን ከመደገፍ በተጨማሪ በንግድ ሥራቸው ከአንድ ሰው በላይ ስለሚቀጥሩ፣ የዚህ ንግድ ብዜት ተጽዕኖ ትኩረት የሚስብ ኾኗል። በአፍሪካ ውስጥ ባሉ ሴቶች የሚመሩ በርካታ ቤተሰቦች ዋና የገቢ ምንጭም ይኸው መደበኛ ያልሆነ ቀጣናዊ ንግድ ነው።

ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ምን ምን ነበሩ?

እንደ ተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) መረጃ፣ በሴቶች ባለቤትነት እና መሪነት የሚተዳደሩ የንግድ ተቋማት በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ የመሳተፍ አዝማሚያቸው ዝቅተኛ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ የሚሸፍኑት ዓለም አቀፍ ኤክስፖርት 15 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይኽም አብዛኛዎቹ በሴቶች ባለቤትነት የተያዙም ኾኑ የሚተዳደሩ የንግዶች እንቅስቃሴዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚከናወኑ መኾናቸውን ያሳያል።

የአፍሪካ ሴቶች አግሪቢዝነስ ኔትወርክ (AWAN Africa) ውስጥ በሴቶች ባለቤትነት ከተያዘው 3000 መደበኛ የግብርና ንግድ ውስጥ 0.7 በመቶ ብቻ የኾኑት ናቸው በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ተሳታፊ የኾኑት።

እነኚህ አንቀሳቃሾች ለንግዱ ዘርፍ የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ቢኖርም፣ በብዙ የአፍሪካ ቀጣናዎች ውስጥ ያሉ መደበኛ ያልሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ሴት ነጋዴዎች፣ ድንበር አቋርጠው የንግድ ሥራቸውን ለመከወን መደበኛ (ሕጋዊውን) መዋቅር ስለማይጠቀሙ ከዋና ዋና ቀጣናዊ የንግድ ሥርዓቶች ተጠቃሚ ሳይኾኑ ቀርተዋል፡፡ ለአብነት እንኳን ሸቀጦቻቸው እና ነጋዴዎቹ በአህጉሩ በነፃ መዘዋወር የሚችሉበት ዕድል ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በዚህ ብቻ ግን አያበቃም፡፡ ነጋዴዎቹ በመደበኛ ድንበር ዘለል የንግድ ሥርዓት ውስጥ ባለማለፋቸው አሁን ላይ ያለውን የገበያ አማራጭ ለመጠቀም ግንዛቤው እና ተነሳሽነቱ እንዳይኖራቸውም አድርጓል፡፡ ከተለያዩ የንግድ ሥርዓቶች ጋር ተያያዞ ሊያገኟው ይችሉ የነበሩ መብቶች፣ ዋስትናዎች እና እድሎችንም እንዲሁ አጥተዋል፡፡ በተጨማሪም የመረጃ እጦት ሴት ነጋዴዎች ድንበር ሲያቋርጡ ለሚደርስባቸው ትንኮሳ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ የንግድ እንቅስቃሴያቸው ላይ ጉዳት እንዲጋጥም ምክንያት ይኾናል።

የአፍሪካ ሴቶች አግሪቢዝነስ ኔትወርክ (AWAN Africa) ሴት የግብርና ነጋዴዎች በተለይም ከድንበር ተሻጋሪ ግብይቶች ጋር ተያይዞ የገበያ ተደራሽነታቸውን በእጅጉ የሚገድቡ የደህንነት፣ የእንቅስሴ፣ የፋይናንስ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።

በድንበር አካባቢዎች ግልጽነት የተሞላበት አሠራር ባለመኖሩ፣ በንግድ መረጃ አቅርቦት ውስንነት እና በኢሚግሬሽን መስፈርቶች ምክንያትም አባሎቻችን በርካታ አደጋዎችን ለመጋፈጥ ይገደዳሉ።

ብዙውን ጊዜ ድንበር አካባቢዎች ከሚገኙ ኃላፊዎች በሚደርሱ ተደጋጋሚ የቃል፣ የአካል እና የፆታ ትንኮሳዎች ሰለባም ናቸው።

ምክረ ሐሳብ

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ስምምነት ሰነድ፣ በአፍሪካ ውስጥ ለሚካሔዱ የንግድ እና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትብብሮች መሳለጥ የሰብአዊ መብቶች፣ የፆታ እኩልነት እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ወሳኝ ግብዓቶች መኾናቸውን እውቅና ይሰጣል (AU፣ 2018b)። በተጨማሪም በማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ ዘላቂነት እና አካታችነት እንዲሁም ውጤታማ የፆታ እኩልነት መኖር የስምምነቱ አጠቃላይ ዓላማዎች ናቸው።

ሴት የግብርና ነጋዴዎች በገጠር ከሚኖር ግብርና በላቀ ከፍተኛ ገቢ ስለሚያስገኙ እና ለአነስተኛ አርሶ አደሮች የእሴት ሰንሰለት ለመፈጠርና ለመደገፍ ስለሚያስችሉም በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍ እና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። ይህ ድጋፍ በገጠር ያለውን ሥራ አጥነት በመቀነስ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት እንዲቀንስ እና ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲኖራቸው ያደርጋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) በሁሉም ደረጃዎች መረጃ ለመጋራት ከግሉ ዘርፍ፣ ከንግድ ምክር ቤቶች፣ ከሴት የንግድ ድርጅቶች እና እንደ አፍሪካ ሴቶች አግሪቢዝነስ ኔትወርክ (AWAN Africa) ካሉ የንግድ አውታረ መረቦች ጋር ተጣምሮ መሥራት ይኖርበታል።

የአፍሪካ ሴቶች አግሪቢዝነስ ኔትወርክ (AWAN Africa) ድንበር አቋራጭ ንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሴቶች የሞባይል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ለማሻሻል ከአጋር ድርጅቶች ጋር መስራት ይገባል።

ለሴት ነጋዴዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መንግሥታት የድንበር ጠባቂዎችን ቁጥር እንዲጨምሩ እና ጥበቃውንም እንዲያጠናክሩ፣ በድንበር አካባቢ ያሉ ኃላፊዎችንም በአግባቡ እንዲያሰለጥኑም ያስፈልጋል።

ምንጭ፡- https://awanafrika.org

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...