የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ለሕዳሴ ግድብ “የገንዘብ ድጋፍ” አድርጋለች የሚል እምነት እንዳላቸው ለሁለተኛ ጊዜ አስተያየት ሰጥተዋል።
ፕሬዚደንቱ ለሕዳሴ ግድብ «እንደሚመስለኝ ዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች፤ ግድቡን ከመገንባታቸው በፊት ችግሩን ለምን እንዳልፈቱት አይገባኝም» ብለዋል ። «ሆኖም ናይል ወንዝ ውኃ ሲኖረው ግሩም ነው፤ ዕንደምታውቁት ለግብጻውያን የገቢ ምንጭ እና ሕይወት እጅግ ጠቃሚ ነው፤ የግብጻውያን ሕይወት ነው።
ያን መንጠቅ እጅግ የሚያስደንቅ ነው፤ ሲመስለኝ ያን ችግር በፍጥነት መፍታት አለብን» ሲሉም ተደምጠዋል። ትራምፕ ይህን ያሉት ከትናንት በስቲያ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዋና ጸሐፊ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነዉ።
በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ያለፈው ሐሙስ ማብራሪያ የተጠየቁት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነበያት ጌታቸው ግድቡ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ካለው ቀንሶ በከፍተኛ ርብርብ የተሠራ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው” ብለው ነበር።
ከግድቡ የቀድሞ ተደራዳሪዎች አንደኛው አቶ ፈቅ አሕመድ “ግድቡን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ነው የሠሩት” በማለት ፕራምፕ “ግልጽ የወጣ አድሏዊ ንግግር እያደረጉ ነው” ሲሉ ተችተዋል።
ግብጽ በበኩልዋ ትራምፕ የሕዳሴዉን ግድብ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ተደስታለች። የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ ኧል ሲሲ ትራምፕን “የሰላም ሰው” ብለዋቸዋል።
