የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲ አሁንም በድጋሚ በቀይ ባህር ደህንነት ላይ ያተኮረ መልዕክት ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም አስተላልፈዋል፤ የቀይ ባህርን ደህንነት ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ግብጽ ለሶማሊያ የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉም ቃል ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን መልዕክት በድጋሚ ያስተላለፉት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድን በግብፅ የባህር ጠረፍ ከተማ ኤል አላሜይን ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው፤ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሁለቱ መሪዎች በውይይታቸው ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ለማስቀጠል ቃል ገብተዋል ተብሏል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲን ግብዣ ተከትሎ የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ግብጽ መግባታቸውን፣ መሪዎቹ በሁለቱ ወንድማማች አገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር እና ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የሁለትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቪላ ሶማሊያን ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።
ሁለቱ መሪዎች ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በግብጽ በኩል የወጣው መግለጫ አንደሚያትተው መሪዎቹ የሁለቱን ሀገራት ሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ተስማምተዋል፣ እንዲሁም መሪዎቹ በቀጠናው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን በመጠቆም በተለይም በሶማሊያ ደህንነት እና መረጋጋት ዙሪያ በዝርዝር ተነጋግረዋል ብሏል።
ፕሬዝዳንት አልሲሲ በተደጋጋሚ በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በቀይ ባህር ደህንነት እና መረጋጋት ዙሪያ አስተያየት ሰጡ ወይንም ተወያዩ የሚሉ አገላለጾች መሰማት የጀመሩት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2024 መጀመሪያ ላይ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅናን ለመስጠት፣ ሶማሊላንድ ደግሞ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመፍቀድ መስማማታቸው በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት መፍጠሩ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ዙሪያ ከሁለቱም ወገኖች ምንም አይነት ድምጽ እየተሰማ ባይሆንም ኢትዮጵያውያ በቀጥታ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት አሁንም ከግብፅም ሆነ ከሶማሊያ በኩል በጥርጣሬ እና በስጋት የሚታይ ነው።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ ከግብፅ መሪ ጋር የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. በሶማሊያ ካቢኔ በመጽደቁ የግብፅ ወታደሮችን፣ ወታደራዊ አውሮፕላኖችንና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን በሞቃዲሾ አስፍራለች።
የሁለቱን መሪዎች ውይይት አስመልክቶ ከሶማሊያ በኩል የወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው ሁለቱ መሪዎች በፀጥታ፣ በትምህርት፣ በንግድ፣ በአሳ ሀብት እና በኢነርጂ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ በኤክስ የማህበራዊ ትስሰር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ቁልፍ በሆኑ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች የሶማሊያ እና ግብጽን ግንኙነቶች ለማጠናከር የሚያስችል ዳሰሳ አካሂደናል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እና የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በመካከላቸው የተፈጠረውን አልመግባባት ለመፍታት ያስችላል የተባለ ስምምነት በቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አሸማጋይነት ታህሳስ 2 ቀን 2017 ዓ.ም መፈራረማቸው ይታወሳል።
የአንካራ ስምምነትን ተከትሎ በሶማሊያ የውጭ ጉዳይና አለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር የተመራ የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ መምጣቱ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ለይፋዊ የስራ ጉብኝት የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ/ም ሞቃዲሹ መግባታቸውን የተመለከተ ዘገባም ቀርቧል።
ወደ ሶማሊያ ያመሩት ጠ/ሚ አብይ በሞቃዲሾ አደን አዴ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ጉብኝቱ በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የተደረሰውን የአንካራ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚከወኑ ጥረቶች አካል መሆኑም በወቅቱ ተጠቁሟል።
የሀገሪቱ ጋዜጣ አህራምን ዋቢ በማድረግ ባቀረብነው ዘገባ ፕርዝዳንት አልሲሲ የአፍሪካ ቀንድ ጸጥታና መረጋጋት ጉዳይ የግብጽ ብሔራዊ የጸጥታ ጉዳይ ጋር እጅግ የተሳሰረ ነው ማለታቸው ይታወሳል። አስ
