በምርጫ ቦርድ በተቀመጠው ቀን ገደብ መሰረት ህልውናው ሙሉ በሙሉ ሊሰረዝ ሁለት ሳምንታት የቀሩት ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት)፤ በድጋሚ “ምንም አይነት” ምዝገባ እንደማያካሂድ አስታወቀ።
ፓርቲው ሚያዚያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ “አደራዳሪዎች፣ የአፍሪካ ህብረት ፓነል እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሀትን ህጋዊ እውቅና አለመመለስ በስምምነቱ ላይ የሚያስከትለውን አደገኛ መዘዝ ተረድተው የድርሻቸውን እንዲወጡ” ሲል ጠይቋል።
የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ( ህ.ወ.ሓ.ት) ጠቅላላ ጉባዔ ማድረን ጨምሮ “በህግ የተጣለበትን ግዴታዎች ባለመወጣቱ” ለሶስት ወራት ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መታገዱን እና ፓርቲው በሦስት ወራት የዕርምት ዕርምጃ ሳይወስድ ቢቀር የፓርቲው ምዝገባ እንዲሠረዝም መወሰኑ ይታወቃል።
ቦርዱ ፓርቲው እንዲያከናውን ያስቀመጣቸውነ ትዕዛዞች እስካሁን ለመፈጸም ምንም አይነት እንቅስቃሴ እያደረገ የማይታየው ህወሓት በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች በምርጫ ቦርድ የተሰጠው “ዕውቅና ቢሰረዝም ባይሰረዝም ህጋዊ ፋይዳ የለውም” ሲል መግለጹ ይታወሳል።
ህወሓት ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ባወጣው መግለጫ “በፌደራል መንግስቱ የተሰረዘው እውቅናየ በፕሪቶርያ ከሰላም ስምምነቱ ጋር ተመልሷል፤ ለሰላም ካለን ፍላጎት በመነሳት የድርጅታችን እውቅና በይፋ እንዲመለስ ለማድረግ ነው ከፌደራል መንግስት ጋር በተደጋጋሚ ስነጋገር የነበረው” ብሏል።
“የፌደራል መንግስት ከፕሪቶርያው ስምምነት ውጭ በሆነ መንገድ በምርጫ ቦርድ በኩል ህወሓትን እንደ አዲስ እንዲመዘገብ ለማድረግ አዋጆችን እና መግለጫዎችን እያወጣ ነው” ሲል ኮንኗል።
በፌደራል መንግስት እየተደረገ ያለው “የፕሪቶርያ ስምምነትን የሚጥስ አካሄድ በተመለከተ ህወሓት ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት ፓኔል መውሰዱን” ያስታወቀሰው መግለጫው “ፓኔሉም የህወሓት ህጋዊ ሰውነት እንዲመለስ እና እንደአዲስ መመዝገብ እንደማይገባው በመግለጽ ውጤቱም እስከ ቀጣዩ የፓኔሉ ስብሰባ ተጠናቆ እንዲቆይ ሃሳብ ሰጥቶበታል” ብሏል።
“ነገር ግን ፓኔሉ እስካሁን ባለመሰብሰቡ በአጠቃላይ የስምምነቱ አፈጻጸም ሆነ የሚታዩ ጥሰቶችን መግምገም አለመቻሉን” አመላክቷል።
“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲያችንን ህወሓትን የማይመለከቱ አዋጆችን በመጥቀስ መግለጫ በማውጣት ተጠምዷል” ሲል የኮነነው መግለጫው “በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት እውቅና ለማግኘት በሚል የትግራይን ህዝብ ትግል እንዲኮላሽ አላደርግም” ብሏል።
የፌደራል መንግስት ከፕሪቶሪያ ስምምነት የወጡ እና በምርጫ ቦርድ በኩል መግለጫዎች ከመስጠት እንዲቆጠብ የጠየቀው ህወሓት” ለስምምነቱ መፈጸም በሚጠቅም መልኩ የሰረዘውን የፓርቲውን ህልውና ሊመልስ ይገባል” ሲል አሳስቧል። አስ
