ለምርጫ የተሠጠ ምስክርነት

Date:

የዚች አጭር መጣጥፍ ተደራሲዎች የህግ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ሌሎቻችሁም ብታነቡት ግን አይጎዳችሁም፡፡

ታህሳስ 2001፤ የቅንጅት ወራሽ ብለን ያቋቋምነው አንድነት ለዴሞክራሲ እና ፍትሕ ፓርቲ መሬት እንዲቆነጥጥ ከላይ ታች እያልኩ ሳለሁ የዘመኑ መንግስታችን ከየት መጣ ሳልል ለሌላ ዙር ዘብጥያ አጭቶኝ ኖሮ አጠዳድፎ ቃሊቲ ወረወረኝ፡፡

የዚህኛው እስር ሁኔታ ከመጀመሪያው እስር እጅጉን የተለየ ነበር፡፡ እንደገባሁ እንደ ቀድሞው እስሬ ከመደበኛ ታሳሪጋ መቀላቀል ቀርቶ ለእስር የተዘጋጀ ማረፊያም አላገኘሁም፡፡ ከእስር ቤቱ ሀላፊ ቢሮ ፊት ለፊት ያለው አንድ ቢሮ ውስጥ አልጋ አስገብተው ከረቸሙብኝ፡፡ ከምኑም በላይ አንዳች ዓይነት የህግ ስርዓትን ሳይከተሉ እድሜ ልክ እስራትን ያህል ነገር እንደ ዘበት የጫኑብኝ ነገር እንደ እግር እሳት አንገበገበኝ፡፡

ይለይልሽ ብለው የዘመድ ቀን መጠየቂያ ቀን ሲደርስ ከደካማዋ አሮጊት እናቴ እና ክፉና ደጉን ካለየችው የሶስት ዓመት ህጻን ልጄ ሀልዬ በስተቀር ማንም እንዳይጠይቀኝ ፈረዱብኝ።

በዳኝነት፣ በጠበቃነት እና በእስረኝነት ዘመኔ ያካመቸሁት መረጃ የሚያሳየኝ በከርቸሌም ሆነ በቃሊቲ እስር ቤት ለረጅም ጊዜ ለብቻው የታሰረው የደህንነት አለቃ የነበረውን ክንፈ ገብረ መድህንን የገደለው ሻለቃ ጸሀዬ (ኋላ የተገደለው) ብቻ ስለነበረ በጥቂት ቀናት ወደ መደበኛው የእስር ከፍል ይወስዱኛል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ አልሆነም! ለካንስ አሳሪዎቼ የወራት የብቻ እስር አቅደውልኛል፡፡

ይህ መሆኑ በደንብ የገባኝ መጀመሪያ ከታሰርኩበት ክፍል ጀርባ የነበረን የቢሮዎች ቅጥያ በተፋጠነ ስራ በቆርቆሮ አጥር በጠባቡ አጥረው፣ አጠገቡ ትንሽ ሽንት ቤት ገንብተው ወደዛ ሲያዛውሩኝ ነው፡፡

በህግ ባለሙያነቴ ላይ የመብት ታጋይነቴ ተጨምሮበት ይህንን በደሌን የፍርድ አደባባይ ሳላሳየው መተው እጅጉን ከበደኝ፡፡ በቅንጅት እስር ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጠበቆች ለእኛ ጉዳይ ፍርድ ቤት በመቆማቸው የጠበቃ ማህበሩ ሳይቀር ብዙ አስተዳደራዊ በደል እንደደረሰበት ስለማውቅ፣ የአሁኑን ጉዳዬን የሚይዝ ጠበቃ የመንግስት ጥቃት ሰለባ እንደሚሆን ስለማውቅ ‘ማንን ጥብቅና ቁምልኝ ልበል?’በሚል በጣም ተጨነቅኩ፡፡

ያም ሆኖ እስሬንም ሆነ የእስሩን ሁኔታ ዝም ብዬ መቀበል የማይታሰብ ሆነና የመከራዬ ተጋሪ እንዲሆን ጠበቃ ተስፋዬ ደረሰን ቃሊቲ አስጠራሁት፡፡


ከተስፋዬ ጋር በዳኝነት አብረን ሰርተናል፤ኋላም ተመስገን ገብረ ስላሴን ጨምረን በጋራ የጥብቅና ቢሮ ከፍተን በጋራ አገልግሎት ሰጥተናል፡፡ ለፍትህ ያለውን ውግንና እና ለጓደኝነት ያለውን ታማኝነት አውቃለሁና ተስፋዬ ለጥያቄዬ እንቢ እንደማይል አውቃለሁ፡፡


በአንዱ እሁድ በእናቴ መልእክት ልኬበት እሮብ ጠበቃ ቢሮ አስጠራኝ ፡፡ አትርሱ የብቻ ታሳሪ ነኝ እና የሰው ትንፋሽ እና የሰው ድምጽ ይናፍቀኛል፡፡ ከሰውም ጓደኛዬን ሳይ ደስ ያለኝ ደስታ መገለጫም የለው፡፡ብዙ ብዙ ነገር አወራን፣ የእስሬን ህጋዊነት ለማስረዳት ሁለት የህግ ሰዎች እንደተሰማሩም ነገረኝ -ጌታቸው ረዳ በአዲስ ነገር ጋዜጣ ተከታታይ ጽሁፍ በመጻፍ፣ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ባለሟሉ ሽመልስ ከማል በመንግስት ሚዲያ በመለፈፍ፡፡ (ይህን በደል አልረሳሁም፤ ይቅር ግን ብያለሁ)፡፡


እኔ እና ተስፋዬ አሳሪዎቼ የፈቀዱልንን ጥቂት ጊዜ ተጠቅመን የድጋሚ የእስሬን ህጋዊነት፣ ይቅርታው የተነሳበትን ሁኔታ ልንሞግት ተስማማን። በሚቀጥለው ሳምንት ተመልሶ እንደሚመጣ ነግሮኝ ተሰናበትን፡፡ ከዛ በኋላ ግን ተስፋዬ ቃሊቲን መርገጥ ተከለከለ፡፡

ተከለከልኩ ብሎ ግን ጉዳዬን አልተወውም፡፡ በጠበቃዬ ፣ በቤተሰቤ ወዘተ የመጎብኘነት መብቴ መሰረት አድርጎ በስሜ ክስ አቀረበ። ክሱን መስርቶ ይህንኑ እንዲነግረኝ ሌላው ጓደኛችንን ቸርነት ወርዶፋን ቃሊቲ ላከው፣ ቸርነትንም ከአንድ ቀን በላይ ባላየውም፡፡


ከ22 ወራት እስር በኋላ ከእስር ጉድጓዴ ወጥቼ ተስፋዬ እኔን ወክሎ ለመሞገት ያደረገውን በዝርዝር ሰማሁ ፤ አነበብሁም፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱን ተቀብሎ በዳኛ ታገል በኩል ፍርድ ቢሰጥም ለማስፈጸም ግን አልተቻለም። ይሁን እንጂ ተስፋዬ ስለ በደሌ እና ስለገጠመኝ ኢ-ፍትሐዊነት ስነ ምግባር እና እውነተኝነትን በተከተለ ሁኔታ በየጋዜጣው እና ሬዲዮ ቀርቦ አብራርቷል፡፡


በእኔ መፈታት ሁላችንም እፎይታ ቢሰማንም በእኔ ዳፋ ተስፋዬ ላይ የተፈጸመው በደል ግን ገና መጀመሩ ነበር፡፡ ስለ እኔ ሆኖ ክስ ማቅረቡ ፣ ማስወሰኑ ሲጠይቅም መግለጫ መስጠቱ እንደ በደል ታይቶ፣ የማረሚያ ቤቱን ስም አጠፋ ተብሎ ሰርቶ የሚኖርበትን የጥብቅና ስራ እንዲያቆም የዲስፕሊን ክስ ተመሰረተበት፡፡ ይሄ ሁኔታ ከእርሱ ይልቅ ለእኔ አስጨናቂ አልነበረም ብላችሁ ነው? እሱ በሙሉ ልቡ ለመብት እና ለፍትህ በመቆሙ የሚደርስበትን ለመቀበል ተዘጋጅቷል ፡፡


ነገሩ ግን ቶሎ የሚቆም አልሆነም። ያሳለፍነው መከራ ሳያንስ እኔም ወንድሜም ፍትሕ ሚኒስቴር የዲሲፕሊን ኮሚቴው ዘንድ ቀርበን መሰከርን። ጉዳዩ ለምርምራ ተብሎ እንደተንጠለጠለ ምንም ሳይባልበት የመንግስት ለውጥ መጣ።


ለህግ ያለው ታማኝነት መስዋእትነት እስከ መቀበል የሚዘልቀው ፣ በአስከፊው ግዜ በሙያው ከጎኔ ለመቆም ያላንገራገረው የቀድሞ የስራባልደረባዬ አቶ ተስፋዬ ደረሰ አሁን የፌዴራል ጠበቆች ማህበርን በፕሬዜዳንትነት ለመመምራት እየተወዳደረ ይገኛል፡፡ እርግጠኛ ነኝ የእያንዳንዱን ጠበቃ መብት ለማስከበር ግምባሩን ሳያጥፍ ይቆማል።
በቀድሞ የምርጫ አስተዳዳሪነቴ፣ መራጭ የሚበጀውን ለመምረጥ እውነተኛ መረጃ ማግኘቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ስለማውቅ ይቺን ምስክርነቴን ለመራጮቹ (ለፌዴራል ፍርድ ት ጠበቆች) ማካፈልን ወደድኩ፡፡

ፍትሀዊ የሆነ ውድድር እና እውነተኛ ምርጫ እንዲኖራችሁ ያለኝን ምኞትም እገልጻለሁ።

ብርቱካን ሚደቅሳ እንደፃፉት!..

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአህጉሪቱን የርስ በርስ ንግድ ልውውጥ 250 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቀደ

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ፀሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ...

በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ክፍያ መፈጸም አይጠበቅባቸውም

አሜሪካ እና ኢራን በተስማሙበት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በሆርሙዝ ወሽመጥ...

እስራኤል ጦሯ በደቡብ ሊባኖስ እንደሚቆይ አስታወቀች

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ እንደተናገሩት፤ በአሜሪካ እና በኢራን...

ኧረ ፋታ ስጡን?!

መንግስት ግን" ምን ሁኑ ?" ሊለን ነው :: አጀንዳ...