የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የስንዴ ምርት አቀነባባሪ አምራቾች ለሚያደርጉት የስንዴ ግዥ የሚፈጸም ክፍያ ላይ የነበረው የ2% ቅድመ ግብር ክፍያ ሥርዓት ተፈጻሚ እንዳይሆን መወሰኑን አስታወቀ።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው የስንዴ አቀነባባሪ አምራቾች በግዥ ወቅት ለሚከፍሉት ቅድመ ክፍያ፣ ታክስ ባለስልጣኑ ሻጮቹ ደረሰኝ መስጠት ስለማይገደዱ ግብይቱን ውድቅ በማድረግ ከፍተኛ ግብር እየጠየቀ ነው በሚል ለብሔራዊ ኢንዱስትሪው ካውንስል ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት መሆኑ ተጠቁሟል።
ችግሩን ለመፍታት የተቋቋመው የጥናት ኮሚቴ ያቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከወር በፊት በተጻፈ ደብዳቤ ውሳኔ አስተላልፏል።
ይህን ተከትሎ ለስንዴ ግዥ የሚፈጸም ክፍያ የቅድመ ግብር ክፍያ ሥርዓት ተፈጻሚ እንዳይሆን የተወሰነ ሲሆን ውሳኔውም በታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ጽ/ቤት በሂደት ላይ ባሉና በቀጣይ ኦዲት ሥራዎች ተፈጻሚ እንዲደረግ ታዟል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ከሰሞኑ በላከዉ ሰርኩላር ላይ እንደተመላከተዉ ፤ የገንዘብ ሚኒስትር ዉሳኔ መሰረት በግዥ ማረጋገጫ የተፈጸመ ግብይት በሌሎች መረጃዎች እየተረጋገጠ ወጪውን የሚያዝበት ሥርዓት በታክስ ባለስልጣኑ በኩል እንዲዘረጋ አሳስቧል።
CapitalNews
