የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ አሁን ላይ ካለበት መቀዝቀዝ ወጥቶ ዳግም እንዲያንሰራራ ትልቁ እንቅፋት እየሆነ ያለው የፋይናንስ እጥረት ሳይሆን፣ ፋብሪካዎች ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ መስፈርቶችን ማሟላት አለመቻላቸው እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢንዱስትሪ ሚኒስትር የዉጪ ምርቶች ተወዳዳሪነት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘሪሁን ፤ ብዙዎች ፋይናንስን እንደ ዋነኛ ችግር ቢያነሱም፣ እንደ ሚኒስቴሩ ግምገማ ግን የፋይናንስ ጉዳይ ከኢንቨስትመንት አዋጭነት በኋላ የሚመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
“አንድ ኢንቨስትመንት አዋጭ እና መስፈርቱን የሚያሟላ እስከሆነ ድረስ ባንኮች ብድር አይከለክሉም፤ ነገር ግን ፋብሪካዎቹ ዓለም አቀፍ ጥብቅ የአካባቢ ጥበቃ ደንቦችን ማሟላት አለመቻላቸው ዘርፉን አዋጭነቱን ጥያቄ ውስጥ ከቶታል” ብለዋል።
አቶ ዘሪሁን አክለውም፣ ቀደም ሲል በርካታ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም አሁን ላይ ውጤታማ ሆነው እየሰሩ ያሉት ጥቂቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ይህም የሆነው የቆዳ ፋብሪካዎች በባህሪያቸው ከፍተኛ የአካባቢ ብክለት የሚያስከትሉ በመሆናቸው እና ይህንን ለመከላከል የሚጠየቁ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃዎችን ማሟላት ባለመቻላቸው እንደሆነ ተመላክቷል።
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት በሞጆ ከተማ “ሞጆ ሌዘር ሲቲ” የተሰኘ የኢንዱስትሪ መንደር እያለማ መሆኑን አቶ ዘሪሁን አስታውሰዋል። ይህ ፕሮጀክት የዘርፉ ተዋናዮች የጋራ የቆሻሻ ማከሚያ ፋብሪካ እንዲኖራቸው በማድረግ፣ ወጪያቸውን እንዲቀንሱና ዓለም አቀፍ ገዢዎች የሚጠይቁትን መስፈርት እንዲያሟሉ ያስችላቸዋል ተብሏል።
ይህ የተነገረው፤ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኀበር ለ15ኛ ጊዜ የሚያካሂደውን የመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርዒት ሜሴ ፍራንክፈርት ከሚባል መሰረቱን ጀርመን ሀገር ካደረገ አለም አቀፍ ንግድ ትርዒት አዘጋጅ ጋር በጋራ ለማከናወን ከስምምነት ላይ መድረሳቸው በተገለፀበት ወቅት ነዉ።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዘላለም መርአዊ እንደገለጹት፣ የቆዳ ኢንዱስትሪው ቀደም ሲል ከቡና ቀጥሎ ለሀገሪቱ ትልቅ የውጭ ምንዛሬ ያስገኝ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ይገኛል።
በአሁኑ ሰዓት ዘርፉ በዓመት ወደ 30 እና 40 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ሲሆን፣ በተቃራኒው ደግሞ የመከላከያ እና የፖሊስ ጫማዎችን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ምርትን በመተካት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ይሁን እንጂ በየአካባቢው የሚጣለው ቆዳ እና ፋብሪካዎች የሚያነሱት የጥሬ ዕቃ እጥረት ቅራኔ ሆኖ መቀጠሉ ተገልጿል።
አቶ ዘላለም እንደ ‘ሜሴ ፍራንክፈርት’ ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች፣ ኢትዮጵያ ከጥሬ ዕቃ አቅራቢነት ወደ ተጠናቀቁ ምርቶች አምራችነት እያደረገች ያለችውን ሽግግር ለማሳየት መድረክ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
