በትግራይ ክልል የትምህርቱን ዘርፍ መልሶ ለመገንባት የሚከተሉት የፖሊሲ አማራጮች የቀረቡትን የድርጊት መርሀግብሮች ተግባራዊ ለማድረግ አማራጭ ስልቶችን ያስቀምጣሉ፡፡
የፖሊሲ አማራጭ 1፡ በትግራይ ክልል አስቸኳይ የትምህረት ቤት ምገባ ፕሮግራም ግባራዊ ማድረግ
እድሎች፡-
የተሻሻለ የተማሪዎች ተሳትፎና ምዝገባ እንዲኖር ያስችላል፡- የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በግጭት በተጎዱ አካባቢ ዋንኛ የትምህርት ተሳትፎን የሚያቀጭጨውን የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ወደ ትምህርት ቤቶች ቀርበው የሚመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር አንዲጨምርና በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዲዘልቁ ያስችላል፡፡
የተማሪዎችን ጤናና ትኩረት ያጎብታል፡- ተማሪዎች ቢያንስ አንድ ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ ካገኙ ጤናቸው ከመሻሻሉም በላይ በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል፡፡
ወላጆችን ያበረታታል፡- በተለይ ትምህርት ቅድሚያ በማይስጥባቸውና የጦርነት አሻራ ትኩስ በሆነባቸው አካባቢዎች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞች ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ያበረታታሉ፡፡
የማህበረሰብ ተሳትፎን ያጎለብታሉ፡- በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም የአካባቢው ማህበረሰብ በምግብ አቅርቦት ሰንሰለትና በምግብ ዝግጅት እንዲሳተፍ ማድረግ ወጪ እንዲቀንስ ከመድረጉም በላይ የማህበረሰቡንና የትምህርት ስርአቱን ትስስር ያጠናክራል፡፡
ስጋቶች
ከፍተኛ ወጪ ሊያስከትል ይችላል፡- መጠነ ሰፊ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እውን ለማድረግ በመጠኑ ከፍ ያለ የገንዘብ አቅርቦት ምንጭ የሚጠይቅ በመሆኑ ፕሮግራሙን ተግባረዊ ማድረግ ውድ ሊሆን ይችላል፡፡
አተገባበሩ ፈታኝ ሊሆን ይችላል፡- ከፍተኛ የዋጋ ንረትና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማግኘት ፈታኝ በሆነበት፣ በተለይም ጦርነት ባደቀቃቸው አካባቢዎች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞችን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡
የጥገኝነት መንፈስ ሊያዳብር ይችላል፡- የፕሮግራሙን ዘላቂነት ለረጅም ጊዜ በማያረጋግጥ መልኩ በውጭ እርዳታ ጥገኛ የመሆን አደጋም ሊፈጥር ይችላል፡፡
የፖሊሲ አማራጭ 2፡ በማህበረሰቡ የሚመራ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ
ዕድሎች፡-
ወጪ ለመቀነስ ያስችላል፡- የአካባቢው ገበሬዎች የሰብል ምርት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱና በምግብ ዝግጅት እንዲሳተፉ በማድረግ የፕሮግራሙን ወጪ መቀነስ ይቻላል፡፡
የማህበረሰቡን ተሳትፎ ያጠናክራል፡- ማህበረሰቡን በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ማሳተፍ የባለቤትንትና የሀላፊነት መንፈስ በመፍጠር የፕሮግራሙን ዘላቂነት ያረጋግጣል፡፡
ከትምህርት ውጪ ያሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ድጋፍ ያደርጋል፡- በማህበረሰቡ የሚመሩ ይህን መሰል ፕሮግራሞች ለአካባቢ ፍላጎቶች ምላሽ በመስጠት ከትምህርት ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ያግዛሉ፡፡
ስጋቶች፡-
የጥራትና የሽፋን ልዩነት ሲፈጠር ይችላል፡- የማህበረሰብ መር የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ውጤታማነት በማህበረሰቡ የሀብት አቅምና ቁርጠኝነት ይወሰናል፡፡ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ የፕሮግራሙ ጥራትና ሽፋን ዘላቂነት ላይኖረው ይችላል፡፡
የሀብት ውሱንነት ሊያጋጥም ይችላል፡- በጦርነት የተጎዳ ማህበረሰብ ሁለንተነናዊ ችግር ውስጥ ያለ በመሆኑ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን እንዲደግፍ መጠበቅ ከእውነታው ጋር ይጋጫል፡፡
የውጭ ሀብት ድጋፍ ጥገኛ መሆን፡- ይህ በማህበረሰብ የሚመራ ፕሮግራም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከአለም አቀፍ የመንግስታት ማህበራት ድጋፍ የሚያስፈልገው በመሆኑ በፕሮግራሙ ዘላቂነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡
የፖሊሲ አማራጭ 3፡ የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት ለትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እንደ ዋንኛ ገንዘብ ማሰባሰብ ስልት
እደሎች፡
መጠነ ሰፊ ተደራሽነትና ተሳትፎ፡- በተለመደው የገንዘብ ማሰባሰብ ስልት የማይሳተፉትን ጨምሮ የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት በዘመቻ መልክ በጣም ሰፊ የማህበረሰብ ክፍሎችን ሊያዳርስ ይችላል፡፡
የማህበረሰብ ተሳትፎ፡- ማህበረሰቡ ትኩረት ሰጥቶ ለሚያምንበት ተግባር በቀጥታ ስለሚያዋጣ የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት የማህበረሰቡን የባለቤትነት ስሜትንና ተሳትፎን ያጎለብታል፡፡
ስራዎችን በሚያመች መልኩ ለማከናወን ያስችላል፡- የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት የተሰባሰበውን ገንዘብ ለታለመለት አላማ በተቀመጠው ጊዜ ለማከናንና ፕሮግራሙም እያደገ እነዲሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ስጋቶች፡-
ገንዘቡን ለማሰባሰብ እርግጠኛ መሆን ያለመቻል፡- የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት ዘመቻ ሁሌም በታቀደው ልክ ገንዘብ ለማሰባሰብ ስለማያስችል በሀበት አሰባሰብ ረገድ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
ከፍተኛ ወጪ የሚያስፈልገው መሆኑ፡- ውጤታማ የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ ለማስታወቂያ፣ ለግንዛቤ መፍጠሪያና አቅምና ፍላጎት ያላቸውን በጎ አድራጊዎች ለማሳተፍ ጥረትና ጊዜን በማዋል ሀብት ለማሰባሰብ ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል፡፡
እንደተጠበቀው በስፋት ሀብት የማይሰባሰብበት ሁኔታ፡- የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት መጠነ ሰፊ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል ሀበት ለማመንጨት የማያስችል ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት የሚሰባሰበው ሀብት ፕሮግራሙን በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ሳይሆን የጎደለውን ለመሙላት ብቻ የሚያግዝ ይሆናል፡፡
የፖሊሲ አማራጭ 4፡ የግብርና ትምህረትን ከትምህረት ቤት የጓሮ አትክለት ልማት ጋር ማስተሳሰር
እድሎች፡-
ጣምራ ተጠቃሚነት፡- ለገጠር አካባቢዎች አስፈላጊ በሆነ መልኩ ተግባራዊ የግብርና ትምህርት በመስጠት የትምህርት ቤት የጓሮ አትክልት ልማት ትኩስ ምርቶችን እንዲያቀርቡ ያስችላል፡፡
ዘላቂነት፡- ትምህርት ቤቶች ለምገባ የሚያስፈልገውን የተወሰነ ምርት በማምረት የፕሮግራሙን ዘላቂነት ያረጋግጣሉ፡፡
ትምህርታዊ እሴት፡- የግብርና ትምህርትን በካሪኩለም ውስጥ በማቀናጀት ተማሪዎች ጠቃሚ ክህሎትና እውቀት እንዲቀስሙ ያስችላል፡፡
ስጋቶች፡
የስራ ማስጀመሪያ ገንዘብ ይጠይቃል፡- የትምህርት ቤት የጓሮ አትክልት ልማትን ለመመስረትና ለማስቀጠል ለግብርና መሳሪዎች፣ ለዘርና ለስልጠና የሚሆን የስራ ማስጀመሪያ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም ውስን አቅም ብቻ ባለባቸው አካባቢዎች ልማቱን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት ሊሆን ይችላል፡፡
ልማቱን የማስቀጠል ፈተና፡- የትምህርት ቤት የጓሮ አትክልት ልማት ውጤታማነት በተከታታይ እንክብካቤና በዘላቂ ስራ ይወሰናል፡፡ ይህም ውስን ሀብትና አስቸጋሪ የአየር ንብረት ባለበት አካባቢ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ፈታኝ ነው፡፡
የሚገኘው ውጤት ውሱን ሊሆን ይችላል፡- በተለይም በርካታ ተማሪዎች ባሉባቸው ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት የጓሮ አትክልት ልማት ብቻውን የሁሉንም ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ ፍላጎት ማሟላት አይችልም፡፡
የፖሊሲ አማራጭ 5፡ አላማ ተኮር የገንዘብና የምግብ ድጋፍ
እድሎች፡-
አላማ ተኮር ድጋፍ፡- አላማ ተኮር ድጋፍ ቤተሰቦች የገንዘብና የምግብ ድጋፍ አግኝተው የትምህርት ተሳትፎ እንዲጎለብት የሚያስችል ሲሆን ይህም በቀጥታ የትምህርትና የምግብ ፍላጎትን ጥያቄዎችን የሚመልስ ነው፡፡
የአተገባበር አመቺነት፡- ይህ ስልት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ከሚደረግ የትምህርት ቤት ምገባ ይልቅ በተለይም የተለያዩ ግብአቶችን ለማሟላት ፈተና በሆኑ አካባቢዎች ለአተገባበር ምቹ በሆነ መልኩ በቀላሉ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል፡፡
ወዲያውኑ የሚታይ ውጤት፡- የገንዘብና የምግብ ድጋፍ በትምህርት ተሳትፎና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ወዲያው የሚታይ አወንታዊ ውጤት ያስገኛል፡፡
ስጋቶች፡-
ክትትል ለማድረግና አስገዳጅ እርምጃ ለመውሰድ አዳጋች መሆኑ፡- በተለይም በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ክትትል በማድረግ አላማ ተኮር ድጋፉ በትክክል ተግባራዊ ስለመደረጉ ለማረጋገጥ ፈታኝ ነው፡፡
ድጋፉ አለአግባብ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡- የሚሰጠው የገንዘብና የምግብ ድጋፍ የፕሮግራሙን ውጤታማነት በሚጎዳ መልኩ ከትምህርት ተሳፎና ከምግብ አገልግሎት ውጪ ለሌላ ተግባር ሊውል ይችላል፡፡
ተደራሽ ያለመሆን፡- በተለይም በሩቅ ስፍራዎችና የደህንነት ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ድጋፉ በአግባቡ ካልተመራ ፕሮግራሙ ክፉኛ ለችግር ለተጋለጡ የህብተሰብ ክፍሎች ላይደርስ ይችላል፡፡
የፖሊሲ አማራጭ 6፡ ለተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ
እድሎች፡-
የትምህርት አሰጣጥ ክፍተቶችን መሙላት፡- በጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን የረጅም ጊዜ የትምህርት አሰጣጥ ልዩነትን በማጥበብ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ የነበሩባቸውን አመታት በማካካስ ከእድሜ እኩዮቻቸው እኩል እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡
ሁል አቀፍ ድጋፍ፡- የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም የመማሪያ መጻህፈትን በማቅረብ፣ ቴክኒካዊ ድጋፍ በማድርግና ለመምህራን ስልጠና በመስጠት በጦርንት የተጎዱ አካባቢዎችን ህጻናት ፍላጎት የሚያሟላ የላቀ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ ያስችላል፡፡
የህሊና መታወክን ያገናዘበ የትምህርት አሰጣጥ፡- የጦርንት ጥቁር ጠባሳ ላረፈባቸው ተማሪዎች ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ የመንፈስ ጭንቀት የሚስከትለውን መታወክ ከግንዛቤ ያስገባ የመምራን ስልጠና በመስጠት ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢ መፍጠር ያስችላል፡፡
ስጋቶች፡-
ክፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ፡- የገንዘብ ድጋፍን፣ የሰው ሀይል ማሰልጠንን የትምህረት መርጃ መሳሪያዎችን ጨምሮ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግና ማዝለቅ ከፍተኛ ሀብት ይጠይቃል፡፡
ፕሮግራሙን ዘላቂ ለማድረግ ፈታኝ መሆኑ፡- በተለይም ከጦርንት በኋላ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ካለውጪ አካላት ያልተቋረጠ ድጋፍ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራምን የረጅም ጊዜ ዘላቂነትን ማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው፡፡
አናሳ የማህበረሰብ ግንዛቤ፡- ኣናሳ የማህበረሰብ ግንዛቤና ተሳትፎ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራምን ውጤታማነት ሊያሰናክል ይችላል፡፡
- ምክረ ሀሳቦች
የትግራይ ክልልን የትምህርት ዘርፍ ቀውስ ለመፍታት የሚከተሉት ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡
አስቸኳይ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረገ፡- በክልሉ ርዕሰ መምህራንና መምህራን አስተያየት መሰረት በድረቅና ርሀብ ምክንያት የተዳከመውን የተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎና ክትትል ለማጎልበት የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረገ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም ለተማሪዎች ቢያንስ በቀን አንዴ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ በትምህርታቸው ላይ ትኩረት አንዲያደርጉና ጤናቸው እንዲሻሻልና እንዲጠበቅ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ፕሮግራሙ በተለይ በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎችና ትምህርት በአንገብጋቢነት ቅድሚያ በማይሰጥበት ሁኔታ ወላጆች ልጆቻቻውን ወደ ትምህርት ቤት አንዲልኩ ማበረታቻ ይሆናል፡፡ በክልሉ መንግስት የተደረገ የዳሰሳ ምልከታ እንዳረጋገጠው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተግባራዊ በተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ከሌላቸው ትምህርት ቤቶች ጋር ሲወዳደሩ የተማሪዎች ተሳትፎና የትምህርት ክትትል ተሻሽሎ ተገኝቷል፡፡
ይህ ምክረ ሀሳብ በዋነኛነት የቀረበው መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችና ለአለም አቀፍ የመንግስታት ድርጅቶች ቢሆንም ምክረ ሀሳቡ ለፌዴራልና ለክልል መንግስታት ጭምር ጥሪ የሚያቀርብ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍና የዲያስፖራውም ተሳትፎ ለፕሮግራሙ ውጤታማነት አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ፕሮግራሙን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታና ወጪው የሚጠበቅና ፈታኝ ቢሆንም ከችግሩ አንገብጋቢነት አንጻር በተባበረ ጥረት የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን ተግባራዊ ማድረገ ይቻላል፡፡ በስራ ላይ ያሉትን የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞች ማስፋፋት እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞችን ከትምህርት ስርአቱ ጋር ማቀናጀት ተገቢ ነው፡፡
የአካባቢ ማህበረሰብ ያለውን አቅም በማሰባሰብ በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተግባራዊነት ላይ ወሳኝ ሚና መጫዎት ይችላል፡፡ ለምሳሌ የአካባቢው ገበሬዎችና የማህበረሰብ ቡድኖች በምግብ አቅርቦት ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት ሲችሉ የተማሪ ወላጆች ደግሞ በየተራ በምግብ ዝግጅት በመሳተፍ ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ ስልት የፕሮግራሙን ወጪ በመቀነስና ማህበረሰቡ በትምህርት ዘርፉ ያለውን ተሳትፎ በማጠናከር ያግዛል፡፡ በክልሉ ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና አለም አቀፍ የመንግስታት ማህበራት በማህበረሰብ የሚመራውን የምገባ ፕሮግራም መደገፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ከትመህርት ገበታ ውጪ ባሉበት ሁኔታ ይህን መሰሉ ፕሮግራም የላቀ አወንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡
ተማሪዎችና መምህራን ትኩስ አትክልትና ፍራፍሬ የሚያመርቱበትን አነስተኛ የጓሮ አትክልት ልማት የተቀናጀ እንዲሁን በማስቻል ጤናማ ምግብ እንዲቀርብና ተግባራዊ የግብርና ትምህርት እውቀት በሚያስገኝ መልኩ ጣምራ ጠቀሜታ እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል፡፡ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙና የትምህርት ተሳትፏቸው እንዲዘልቅ የሚረዳው ይህ ፕሮግራም በአካባቢ የግብርና ባለሙያዎችና በመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መደገፍ ይኖርበታል፡፡
የተሟላ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረገ በማይቻልበት ሁኔታ ለወላጆች አላማ ተኮር የገንዘብና የምግብ ድጋፍ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህ አላማ ተኮር የገንዘብና የምግብ ድጋፍ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ በአግባቡ መገኘታቸውን፣ ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውንና ትምህርታቸውን ለመከታታል በሚያስችላቸው መልኩ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ማእከላዊ ዞን 4.8 በመቶ፣ በሰሜን ምእራብ ዞን 12.4 በመቶ ተማሪዎች ብቻ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ሲሆኑ ይህም ፕሮግራሙን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ያመለክታል፡፡
የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን ተግባራዊ ለማደረግ ፈታኝ ለሆነውን የገንዘብ እጦት መፍትሄ ለመስጠት የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት ተግባራዊ ማድረግ አዋጭ ዘዴ ሊሆን ይችላል፡፡ የማህበረሰቡን፣ የዲያስፖራውንና የአለም አቀፉን ድጋፍ የተባባረ አቅም አሟጦ በመጠቀም የብዙሀን ገንዘብ የማሰባሰብ ስልት የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን ለማዝለቅና ለማስፋፋት የሚያስችል ሀብት ለማሰባሰብ ይቻላል፡፡ ይህ ስልት የህጻናት ደህንነትና ትምህርeት ጉዳይ የሚገዳቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች በሰፊው ተሳትፎ እንዲያደርጉና የፕሮግራሙ ባለቤት እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡
የመሰረተ ልማት ጥገናና ማሻሻያ፡- የመሰረተ ልማት ጥገናና ማሻሻያ ጉዳት የደረሰባቸው የትምህርት ቤት መሰረተ ልማቶች ጥገናና መልሶ ግንባታ ቅድሚ መስጠትን ይመለከታል፡፡ ይህ ሂደት አስፈላጊ የትምህርት መርጃ ግብአቶችን ማሟላትና ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሂደት አመቺና ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥን ያካትታል፡፡
የተጠናከረ ድጋፍ ለተፋጠነ ትምህርት ፕሮግራም፡- በትግራይ የትምህርት ዘርፉን መልሶ ማቋቋም ትምህርት ቤቶችን ከመጠገንና ከመገንባት በላይ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ወርቃማ የትምህርት ዘመናቸው ለባከነባቸው ተማሪዎች ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዚህ ተማሪዎች ከእድሜ እኩዮቻቸው እኩል እንዲሆኑና ዳግም ወደ ኋላ እንዳይቀሩ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም በእጅጉ ያግዛቸዋል፡፡ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራምን ለማጠናከር አስፈላጊ የመማሪያ መጻህፍት አቅርቦት፣ ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ መስጠትና ለመምህራን የታቀደ የአቅም ግንባታ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ የተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት መምጣትንና ተሳትፏቸውን ሲያሳድግ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ደግሞ የትምህርት ጥራትን ያረጋግጣል፡፡
መምህራንን በተክክለኛው ዘዴ ማስታጠቅ ከሌላው ድጋፍ ባልተናናሰ መልኩ አስፈላጊ ነው፡፡ የጦርነት ገፈት ቀማሽ ተማሪዎች ፍላጎትን ባማከለ ሁኔታ መምህራንን የመንፈስ ጭንቀት የሚያስከትለውን የህሊና ቀውስ ባገናዘበ መልኩ የማስተማር ዘዴ እንዲካኑ ስልጠና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በዚህም ተማሪዎች ከህሊናቸው የጦርንት ጥቁር ጠባሳ እንዲሽርና በትምህርታቸው እንዲጎብዙ ማገዝ ይቻላል፡፡
የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ተግባራዊ ሲደረግ ፈታኝ እንደሆነ ሁሉ ማህበረሰቡን በፕሮግራሙ ማሳተፍም የዚያኑ ያህል ፈታኝ ነው፡፡ ተሳትፎን ለማጎልበት በሚደረገውም ጥረት የእናቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጎልበት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በፍላጎት ዳሰሳ ጥናት በመመራት ውጤታማ የሀብት ድልድል ማደረግ የስራ ድግግሞሽ እንዳይኖርና ያለውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል፡፡
እንደ ታብሌት ያሉ የኤሌክተሮኒክ ዲጂታል መማሪያ መሳሪያዎችን መጠቀም የተለመደውን የተፋጠነ የትምህረት ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድግ የሚወጣውን ሙሉ የትምህርት ወጪ በመቀነስ ያግዛል፡፡ ይህ ስልት ተማሪዎች ከመምሮቻቸው ድጋፍ እያገኙ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ በራሳቸው ፍጥነት እውቀት እንዲቀስሙ ያስችላቸዋል፡፡
እራስን በራስ ለማስተማር የሚያግዝ የትምህረት መርጃ ማዘጋጀትና ማሰራጨት ተማሪዎች በአነስተኛ የመምራን ድጋፍ በግላቸው ሊጠቀሙበት የሚያስችል በመሆኑ ወጪ ቆጣቢ አማራጭ ነው፡፡ እንዚህ እራስን በራስ ለማስተማር የሚያግዙ የትምህርት መርጃዎች መሰረታዊ የትምህርት ክህሎቶችን፣ ስሌቶችንና ሌሎች ርእሰ ጉዳዮችን የሚሸፍኑ ሆነው ተማሪዎች በራሳቸው ፍጥነት እውቀት አንዲቀስሙና የመምህራንን የሙሉ ጊዜን አርዳታን የማይጠቁ ናቸው፡፡
የትምህርት ሂደቱ ወጤታማ እንዲሆን በእድሜና በእውቀት ሻል ያሉ ተማሪዎች ታናሾቻቸውን የሚያስጠኑበት የአቻ ላቻ የመማማር ስልት ተግባራዊ ማድረግ ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ ስልት ነው፡፡ ይህ ስልት ወደ ኋላ የቀሩትን የመማር ሂደትን የሚያፋጥን ብቻ ሳይሆን የአቻ ላቻ አስጠኚዎችን እውቀትንም ያዳብራል፡፡
ማህበረሰቡን መሰረት ያደረገ የተማሪዎች ምዝገባ ዘመቻ፡- በማህበረሰቡና በትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ግንዛቤ በማሳደግና ተሳትፎን በማበረታታት ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉ እጻናት ለትምህርት እንዲመዘገቡ የታቀደ ዘመቻ ማካሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ ጠንካራ የማህበረሰብ ድጋፍ ስርአት መገንባተም የሂደቱ ወሳኝ ግብአት ነው፡፡ ከወላጆች፣ ከአስተማሪዎችና ከማህበረሰብ መሪዎች የተውጣጣ የአከባቢ ኮሚቴ ለዘመቻው መሳካት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ ኮሚቴው የትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታን ሂደቶችን ይቆጣጠራል፣ የተማሪዎችን እድገትና መሻሻል ይከታተላል፣ በተለይ የሴት ተማሪዎችን ችግሮች ይለያል ፤ መፍትሄ ለመስጠትም ጥረት ያደርጋል፡፡ የኮሚቴ አባላቱ ከባቢያዊ እውቀትና ተጨባጩን ሁኔታ መረዳት ውጤታማና አካታች የትምህርት ስርአት እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ መተኪያ የለውም፡፡
ማህበረሰቡ ለሴት ተማሪዎች ትምህርት በአካባቢ ማህበረሰብና በብሄራዊ ደረጃ ጥብቅና እንዲቆም ማብቃት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ዘላቂ ለውጥ ያስገኛል፡፡ ለልጃገረዶች ትምህርት ስኬት ድምጽ በመሆን የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ቅድሚያ አግኝቶ ሁሉም ህጻናት እኩል እድል አግኝተው እምቅ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ማህበረሰቡ የማይተካ ሚናውን መጫወት ይችላል፡፡ ይህ ማህበረሰቡ ለትምህርቱ ዘርፍ መጎልበት የሚቆመው ጥብቅና ለትግራይ ክልል የትምህርት ስርአት የወደፊት ብሩህ ተስፋ መንገድ ጠራጊ ነው፡፡
በትግራይ ትምህርት ቤቶችን እንደገና ለመክፈትና የትምህርት ስረአቱን ለማስቀጠል ከምናደርገው ጥረት በተጓዳኝ የመንፈስ ጭንቀት የሚያስከትልውን የህሊና መቃወስና የጦርነት ክፉ አሻራ በሂደት ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ ተግተን መስራት አለብን፡፡ ተማሪዎች፣ አስተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ወደ ትምህርት ስርአቱ ሲመለሱ ደህንነት እንዲሰማቸውና ሁለንተናዊ ድጋፉ እንደማይለያቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
የሰው ሀብት ድጋፍን ማጠናከር፡- የመምህራን እጥረትን በተመለከተ አዳዲስ መምህራንን መቅጠርና ለመምራን ያልተከፈላቸውን ደሞዝ በተቻለ መጠን መክፈልና ለችግሩ እልባት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አሁን በስራ ላይ ላሉ መምህራን ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ማድረግና ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡
አጋርነትንና የሀብት ምንጭን ማስፋት፡- ተጨማሪ ሀብት በማግኘት የትምህርቱን ዘርፍ ችግር በገጠመ ጊዜ ሁሉ መደገፍ እንዲቻል ከአለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና መንግስታዊ አካላት ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር፡፡
ሁል አቀፍ የስነ ልቦና ድጋፍ መስጠት፡- በጦርነቱ ምክንያት በተማሪዎችና በመምህራን ላይ የተፈጠረውን የህሊና ቀውስና የመንፈስ ጭንቀት መቋቋም እንዲችሉ የተሟላ ስነ ልቦናዊ ድጋፍና አገልግሎት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ለህጻናት፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለመምህራን ስነ ልቦናዊ ድጋፍና አገልግሎት መስጠት ግዴታም ጭምር ነው፡፡
መደምደሚያ
የትግራይ ክልል የትምህርት ዘርፍ ቀውስ መጠነ ሰፊ በመሆኑ አፋጣኝና ሁል አቀፍ ተግባራዊ ምላሽ ይጠይቃል፡፡ የክልሉን የትምህርት ስረአት መልሶ ለማቋቋምና ለማጠናከር በአስቸኳይ የሚያስፈልገውን ለምግብ ዋስትና ደህንነት፣ ለመሰረተ ልማት ጥገናና ግንባታ እንዲሁም ለትምህርት መርጃ ግብአት ችግሮች መፍትሄ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለሰው ሀይል እጥረትና ለደህንንት ስጋት ፈተናዎች ትኩረት ሰጥቶ መፍታትም አስፈላጊ ነው፡፡
አነዚህን ፈተናዎች ለመቋቋምም ከመንግስት አካላት፣ ከአለም አቀፍ የልማት አጋሮችና ከአካባቢ መህበረሰቦች ጋር የሚደረጉ የትብብር ጥረቶች ወሳኝ ናቸው፡፡ የትግራይ የትምህርት ስረአት መልሶ ተቋቁሞና ተጠናክሮ ለክልሉ ህጻናት የወደፊት ብሩህ ተስፋ ሊያረጋግጥ የሚችለው በተባባረ ስልት ተግባራዊ በሚደረግ ምላሽ ነው፡፡ የጦርነት ውጤት የሆነው የመንፈስ ቀውስን ለመሻር የሚደረገውን ድጋፍ እንዲሁም ማህበሰብ መር ለሆኑ ተነሳሽነቶች የሚሰጠውን ድጋፍ ጨምሮ ሁል አቀፍ ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ዘላቂ ውጤት ያስገኛል፡፡
——-
ምሥጋና፡- ይህ የፖሊሲ መግለጫ ከማላላ ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በኢኒሺየቲቭ አፍሪካ የተዘጋጀ ነው፡፡ ኢኒሺየቲቭ አፍሪካ ከማላላ ፈንድ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በትግራይ የተፋጠነ የትምህርት ፕሮግራም ፕሮጀክትን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በትግራይ ክልል በተለይም በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መልሰው እንዲያገግሙና የተማሪዎች አንገብጋቢ ችግሮች እንዲቀረፉ ለማገዝ ያለመ ነው፡፡
በዳንኤል መኮንን ይልማ
———-
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 219 ሕዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም
