ለአእምሮ ጤና ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ጥያቄ ቀረበ

Date:

የአእምሮ ጤና ትኩረት እንዲሰጠውና በተግባር የተደገፈ ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ጥያቄ ማቅረቡን የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማህበር አስታውቋል።

አሁን ላይ የአዕምሮ ጤና ከሌላው ጊዜ በተሻለ መልኩ ትኩረት እየተሰጠውና ሕብረተሰቡም ግንዛቤ እያገኘ ስለመምጣቱ የተናገሩት የማህበሩ ፕሬዝዳንት እሌኒ ምስጋናው፤ ነገር ግን ግንዛቤ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ በተግባር የተደገፈ ሥራ እንደሚያስፈልግ ለአሐዱ ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት መንግሥት ለአእምሮ ጤና የሚገባውን ያክል በጀት መመደብ እንዳለበት በማንሳት፤ “በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶለት እንዲፀድቅ እንፈልጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህንን ሀሳብም ለጤና ሚኒስቴር ማቅረባቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ ነገር ግን ‘ሌሎች የጤና ዘርፎችን ጨምሮ ያካተተ “የጤና አገልግሎት አዋጅ” እንዲወጣ በማድረግ በአዋጁ ውስጥ የአእምሮ ጤናን በመመሪያ ማካተት ይቻላል’ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።

በዚህ የጤና አገልግሎት አዋጅ ሥር የአእምሮ ጤናን በሚመለከት ወደ 11 አንቀፆች እንዳሉ አንስተው፤ “ይህም የጤና አገልግሎትን ብቻ የተመለከተ ነው” ብለዋል።

በመሆኑም “እኛ የምንሟገተው ግን የአእምሮ ጤና እንደሌሎች ሕመሞች ሳይሆን የአንድን ሰው አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ መንፈሳዊ እና አጠቃላይ የሕይወት እንቅስቃሴውን በሙሉ የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑና በአንድ ጠቅላላ የጤና አዋጅ ሥር እነዚህን ነገሮች በሙሉ ማካተት ስለማይቻል ራሱን የቻለ ሕግ እንዲወጣለት ነው የምንፈልገው” ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የአእምሮ ጤናን በሚመለከት የተለያዩ ሕጎች ላይ የተጠቀሱ ነገሮች መኖራቸውን በማንሳት፤ ለአብነትም የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ላይ ስለአእምሮ ሕመምተኛ የተጠቀሰው ቃል አግባብ ባለመሆኑ መስተካከል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

አክለውም አእምሮ ሕመምተኛው የተጠራበት ስያሜ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ አመለካከት እንዳለው አንስተዋል።

በመሆኑም የአእምሮ ጤና ሕመም ያለባቸው ሰዎች አያያዝን በተመለከተ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ለአብነት ያነሱት ፕሬዝዳንቷ፤ የአእምሮ ጤና ታማሚ ለሆኑ ሰዎች ትምህርት ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ እገዛ እንደሚደረግላቸው ጠቅሰዋል።

በተለይም የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኛ መብቶች ኮንቬንሽን ከጸደቀ ጀምሮ ብዙ ለውጦች መደረጋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ያንን ለውጥ ያገናዘበ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ሕግ የሚፀድቅለት ከሆነም በተለያዩ መንገዶች ለአድሎና መገለል ተጋላጭ የሆኑ የአእምሮ ጤና ታማሚዎችን መብት የሚጠብቅና ለበሽታው ትኩረት ተሰጥቶ የታማሚውን ቁጥር መቀነስ የሚያስችል እንደሚሆን ገልጸዋል።

(አሐዱ ሬድዮ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ድርድር እስኪጠናቀቅ ድረስ የተኩስ አቁሙ መራዘሙን አስታወቁ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፓኪስታን ጥያቄ መሠረት ከኢራን ጋር የገቡትንየተኩስ...

ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ተፈቀደ

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የልማት ክንፍ የሆነው ኢአይቢ ግሎባል (EIB...

ሃይንከን በአልኮል መጠኑ ጠንከር ያለ ቢራ ለኢትዮጵያ ገበያ አስተዋወቀ

ሃይንከን ኢትዮጵያ በእለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን ዴሰፔራዶስ (Desperados)...