ለውጭ አገር ዜጋ ለመኖሪያ ቤት 150 ሺህ ዶላር እንደሚያስፈልገው የሚደነግግ መመሪያ ወጣ

Date:

ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ ላይ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ቢያንስ 150 ሺህ ዶላር እንደሚያስፈልገው የሚደነግግ መመሪያን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አወጣ።

አንድ የውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ የቤት ባለቤት ለመሆን የማኅበረሰብ ሞራል እና መሰል ጉዳዮች ላይ ገደብ የሌለበት መሆን እንዳለበት ተደንግጓል።

በመመሪያው መሠረት የውጭ አገር ዜጋ ማለት፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋን ሳይጨምር ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለው ወይም የሌላ አገር ዜግነት ያለው ማንኛውም ሰው ማለት ነው።

የውጭ አገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አሠራር ለመወሰን የወጣው መመሪያ ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው ሐምሌ ወር የጸደቀ ነው።

በመመሪያው መሠረት ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ሊያሟላ የሚገባው ለአንድ መኖሪያ ቤት የሚያስፈልግ ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን ተዘርዝሯል።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በሸገር ከተማ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ቢያንስ 150 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ያስፈልገዋል።

ሸገር ከተማን ሳይጨምር በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በሶማሌ ክልል፣ በሐረሪ ክልል ወይም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ደግሞ ዝቅተኛው የገንዘብ መጠን 120 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ማቅረብ ነው።

ከሌሎቹ ክልሎች የውጭ አገር ዜጋ የቤት ባለቤት ለመሆን ዝቅተኛ ገንዘብ የሚጠየቀው በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልል ሲሆን የገንዘቡ መጠን ደግሞ 100 ሺህ ዶላር እንደሆነ ተደንግጓል።

አንድ የውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ ሊኖረው የሚችለው የቤት መጠን አንድ ብቻ ነው።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፈቃድ ወስዶ እያለማ ያለ ባለሀብት ግን ይህ ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን ሳይገድበው የአንድ ቤት ባለቤት መሆን ይችላል።

በመመሪያው መሠረት ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ የተጠቀሰውን ለአንድ ቤት የሚያስፈልግ ገንዘብ የሚያስቀምጥበት የባንክ ሂሳብ እንዲከፈትለትና ገንዘቡን በውጭ ምንዛሬ እንዲያስቀምጥ የሚፈቅድ ደብዳቤ ከሚመለከተው መሥሪያ ቤት በማጻፍ በመረጠው ባንክ ገቢ ማድረግ አለበት።

አንድ የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን የሚያስችል ፈቃድ የሚያገኘው፤ የጸና ፓስፖርት ካለው፣ የወንጀል ታሪክ የሌለው ስለመሆኑ ከሚኖርበት አገር ማረጋገጫ ከሚመለከተው አካል ማስረጃ ማቅረብ ከቻለ ነው።

በተጨማሪም ከሀገር ሰላም፣ ደህንነት፣ ጸጥታ፣ የሕዝብ ጥቅም፣ የማኅበረሰብ ሞራል እና መሰል ጉዳዮች ላይ ገደብ የሌለበት መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃም ማቅረብ አለባቸው ይላል መመሪያው።

ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ በመንግሥት ቀጥተኛ ድጎማ ለዜጎች በሚሠሩ የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች ውስጥ የመኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን አይችልም፤ ይህም የቤት ባለቤት በሚሆኑ የውጭ ዜጎች ላይ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ በወጣ አዋጅ የተጣለ ገደብ ነው።

በአዋጁ መሠረት የውጭ አገር ዜጋ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ከሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋም ወይም ምንጭ ገንዘብ መበደር ወይም ካፒታል ማሰባሰብ አይችልም።

በኢትዮጵያ የቤት ባለቤት የሆኑ የውጭ ዜጎችን መብት በተመለከተ ደግሞ መመሪያው ሲዘረዝር ለኢትዮጵያውያን የተሰጡ የንብረት መብቶች ይኖራቸዋል፤ ለግለሰቦች ማከራየት ይችላሉ፣ ለንግድ ዓላማ ማከራየት ግን አይቻልም።

ለራሱ እና ለቤተሰቡ የመኖሪያ ፈቃድ፣ የመግቢያ ቪዛና ኢትዮጵያ መመላለስ እንዲችሉ የሚያደርግ አግባብነት ባለው አካል የሚሰጥ እስከ አምስት ዓመት የሚያገለግል የብዙ ጊዜ መመላለሻ ቪዛ የማግኘት መብት አላቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ እና አሠራር መሠረት ከመኖሪያ ቤቱ በሕጋዊ መንገድ የሚያገኘውን የኪራይ ወይም የሽያጭ ገቢ በወቅቱ ተመን በውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ አገር የማስተላለፍ መብት አለው ይላል አዋጁ።

መመሪያው ታትሞ በፍትሕ ሚኒስቴር ድህረ ገጽ ላይ ከተጫነበት ቀን ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል ይላል።
በፍትሕ ሚኒስቴር ድህረ ገጽ ላይ የተጫነው ባለፈው እሁድ ነሐሴ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ነው።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አቶ ይህንዓለም አቅናው የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆኑ

በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ እና ከፍተኛ የባለአክስዮኖች ቁጥር ካላቸው...

ማዕቀቦች የኢራንን የኒውክሌር መርሃ-ግብር ቢያደናቅፉም መንግስቱን ሊጥሉ እንደማይችሉ ተገለጸ

ማዕቀቦች የኢራንን ወታደራዊ እና የኒውክሌር እንቅስቃሴዎች አስቸጋሪና ውድ እንዲሆኑ...

የአፍሪካ ሀገራት አዲስ የኢንቨስትመንት ፈንድ ይፋ አደረጉ

በአፍሪካ ሀገራት ላይ የተደቀነውን ከፍተኛ የብድር ጫና ለማቃለል እና...

ዶናልድ ትራምፕ “በቅርቡ” ሆርሙዝ የአሜሪካ ግዛት አካል እንደሚሆን ተናገሩ

ከኢራን ጋር ያለው ግጭት እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ሰዓት የአሜሪካው...