በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት የሚገኘው የታላቁና ጥንታዊው የዋልድባ አብረንታንት መድኃኔዓለም ገዳም አባቶች፤ በመላው ዓለም የሚኖሩ ሕዝበ ክርስቲያኖች ለገዳሙ ድጋፍ እንዲያደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዋልድባ አብረንታንት ገዳም ኢትዮጵያ ካሏት መንፈሳዊ ቅርሶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ገዳም ሲሆን፤ በሀገሪቱ ካሉ ገዳሞች በስፋት ትልቁ እና የተለያዮ የሥነ-ፅሁፍ ታሪኮችንና ጥንታዊ ስዕሎችን በውስጡ መያዙን የገዳሙ አባቶች አስታውቀዋል።
በገዳሙ ዙሪያ 11 ወንዞች መኖራቸውን የገለጹት የገዳሙ አባቶች፤ ቦታው የገዳሙ በመሆኑ በቂ የሆነ ምርት ማምረት ባለመቻሉ በገዳሙ የሚገኙ አባቶችን ለመደገፍ የገቢ ማሰባሰቢያው መዘጋጀቱን ተናረዋል።
የዋልድባ ገዳም የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ቀሲስ ኢንጂነር ወንድሙ አበጀ፤ በገዳሙ የተለያዩ የተፈጥሮአዊ ሃብቶች መኖራቸውን የገለጹ ሲሆን፤ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከውጭ የምታስመጣቸውን የእጣን ምርት በገዳሙ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአካባቢው በቂ የሆነ ወንዞች ቢኖሩም ቦታው ተራራማ በመሆኑ ውሃውን ለም ወደ ሆነው አካባቢ በማዳረስሰ በቂ የሆነ ልማት በገዳሙ ለማልማት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን የገለጹም ሲሆን፤ በተጨማሪም በአካባቢው ሰፊ ትምህርት ለማስጀመር መታቀዱን ተናግረዋል።
በዋልድባ አብረንታንት ገዳም 1 ሺሕ 500 አባቶች እንደሚገኙና ገዳሙ በኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያ በስደቱ ወራት በኋላም በ485 ዓ.ም መጋቢት 27 እንደተመሠረተ ገልጸዋል፡፡
ለገዳሙ የሚደረገው ድጋፍ ለአባቶች ብቻ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያንእና ለምእመናን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል።
ገዳሙ 400 ሄክታር እንደሚገኝ እና ይህን ቦታ በማልማት ቤተክርስቲያን እና ገዳሙን መደገፍ እንደሚገባ የተገለጸም ሲሆን፤ ይህን ለማሳካት የገቢ ማሰባሰቢያ መረሃ ግብሩ ታሕሳስ 5 ቀን እንደሚጀምር ቀሲስ ኢንጂነር ወንድሙ አበጀ አስታውቀዋል፡፡ ስለሆነም በዓለም የሚገኝ ህዝበ ክርስቲያን ለገዳሙ ድጋፍ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በገዳሙ ያሉትን መሰረታዊ የልማት ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ ለማከናወን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት በተሰጠው ፍቃድ ቁጥር 3363/177/2017 መሰረት፤ የዋልድባ አብረንታንት መድኃኔዓለም ገዳም ዘአቡነ ሚናስ ማኅበር መቋቋሙም ተነግሯል።
