ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ ከሉሚና ቴክኖሎጂስ ኃ.የተ.የግ.ማ. ጋር በመሆን ሉሚና የተሰኘ ዲጂታል የሕይወት መድን መተግበሪያ በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
መተግበሪያው ለዘመናት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ተወስኖ የኖረውን የመድን ፖሊሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደሀገራችን 4 ቋንቋዎች (ማለትም ወደአማርኛ፥ አፋን ኦሮሞ፥ አፍ ሶማሊ እና ትግርኛ) በመተርጎም ማንኛውም ሰው የመድን ውሉን አንብቦ በመረዳት ከ100 ሺህ እስከ 750 መቶ ሺህ ብር የሕይወት መድን እንዲገዛ ለማድረግ ታስቦ የበለጸገ እንደሆነ ተነግሯል።
ሉሚና ደንበኛው በህይወት ባይኖር እንኳን ሕጋዊው የደንበኛው ወራሽ የካሳ ክፍያ ጥያቄውን በመተግበሪያው ወዲያኑ ማቅረብ እንደሚችል ፣ ወራሹ አስፈላጊ ሰነዶችን በማሟላት አጠራጣሪነት ከሌለው በመተግበሪያው በአንድ ቀን የሚከፈለው ሲሆን ነገር ግን የካሳ ሰነዶቹን ማጣራት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ካሳ ተቀባዩ በአቅራቢያው በሚገኝ የኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ ቅርንጫፍ ወይም ውክልና ከተሰጣቸው ተቋማት በአካል ሲቀርብ ከ2 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ክፍያው ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል።
የሉሚና መተግበሪያ በኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ ከሉሚና ቴክኖሎጂስ ኃ.የተ.የግ.ማ. ጋር በፈጠሩት ጥምረት ወደሥራ ሲገባ በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በዘርፉ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጠር የተገለፀ ሲሆን መተግበሪያው በሁለት ኩባንያዎች ጥምረት በ5 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለ3.2 ሚሊዬን ኢትዮጵያዊያን የግለሰብ የሕይወት መድን ሽፋን በመስጠት የሞት ስጋታቸውን እንደሚፈታ፥ ከ13 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መልኩ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር፥ በጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) ላይ የ0.024% ዕድገት እንደሚያመጣ እና የሀገሪቱ Insurance Density ላይ ደግሞ የ0.36$ ጭማሪ እንደሚያሳይ ይጠበቃል ተብሏል።
(ድሬቲዩብ)
