ሌሎች ዘርፎች እያሉ ለምን ለቱሪዝም ይሄ ሁሉ ብር ይፈሳል ?

Date:

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኤንቢሲ ቴሌቪዥን ከጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ጋር  ” አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር ” በሚል ስለ ቱሪዝም ቃለምልልስ አድርገዋል።

በዚህም ወቅት፣ ” መንግሥት ሌሎች ዘርፎች እያሉ ለምን ይሄ ሁሉ ሃብት፣ ይሄ ሁሉ ብር፣ ይሄ ሁሉ መዋለነዋይ ቱሪዝም ላይ ያፈሳል ? ” በሚል ስለሚነሳው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠይቀው መልሰዋል።

መንግሥት በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መዋለ-ነዋይ (Investment) እያፈሰሰ የሚገኘው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ብዝሃ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ “ግብርና መር” በሆነ ነጠላ የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ የተንተራሰ ኢኮኖሚ መገንባት ታስብ እንደነበር  ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ አካሄድ ግን እራሱ ግብርናውን እንኳን በበቂ ደረጃ እንዳላሳደገው ፤ ሌሎች ዘርፎችንም ማንቀሳቀስ እንዳልቻለ ገልጸዋል።

በአንድ ዘርፍ ብቻ የተንተራሰ አካሄድ በአጭር ጊዜ የሚፈለገውን የእድገትና የብልፅግና ውጤት እንደማያመጣ ፤ ሀገርን እንደማያበለጽግ አመልክተዋል።

በመሆኑም መንግሥት ሰፊ ጊዜ ወስዶ ባደረገው ጥናት፣ ፈጣንና ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ተመላሽ (Return on Investment) ከሚያስገኝ የብዝሃ-ዘርፍ ስትራቴጂ ውስጥ ቱሪዝምን ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ መምረጡን አስታውቀዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ እስከ 12.6 ትሪሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበት የቱሪዝም ዘርፍ፣ ለኢትዮጵያ ግዙፍ የውጭ ምንዛሬና የሀብት ምንጭ የመሆን አቅም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በዘርፉ የሚንቀሳቀሰውን ግዙፍ ሀብት በምሳሌ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፦
– አሜሪካ በዓመት እስከ 215 ቢሊዮን ዶላር፣
– ስፔን 107 ቢሊዮን ዶላር፣
– ታይላንድ እስከ 95 ቢሊዮን ዶላር፣
– በአፍሪካ ግብፅ ከ14 እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያገኙ ጠቅሰዋል።

ይህንን ዓለም አቀፋዊ ታላቅ ሀብት ኢትዮጵያ ተገቢውን ድርሻ መቋደስ መቻሏ በሌሎች ዘርፎች ለምታደርገው እንቅስቃሴ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ስለ ጎብኚዎች ቁጥርም ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዓመት ፈረንሳይን እስከ 102 ሚሊዮን፣ ሜክሲኮን ወደ 97 ሚሊዮን፣ ማሌዥያን 40 ሚሊዮን እንዲሁም ሞሮኮን እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚጎበኙ ጠቅሰዋል። ይህ ቁጥር ትልቅ የገበያ ዕድል እንዳለውም አስረድተዋል።

” የመጣው ሰው እውቀት ያመጣል፣ ይሸምታል ፣ ይዛመዳል፣ ኢንቨስት ያደርጋል ብዙ ጠቀሜታ አብሮት ይመጣል ” ብለዋል።

ሌላው ቱሪዝሙ እጅግ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅም ያለው ዘርፍ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አብራርተዋል።

በዓለም ላይ ከ370 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቱሪዝም እንደሚቀጠሩ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ” ከዚህች ውስጥ የተወሰነች ፐርሰንት ብንጋራ የኛን ሁኔታ ይቀይራል፥ በአመት 10.9 ስራ የሚገኘው ከቱሪዝም ሴክተር ነው 10% ስራ ከቱሪዝም አገኘን ማለት ሌላ 10% ከሌሎች ዘርፎች ካገኘን ሲሰናሰል በስራ ዘርፍ ያለውን እጥረት ሊቀርፍና የስራ ፍላጎት ሊያሟላ ይችላል ” ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ፣ ቱሪስቶች ወደ ሀገር ሲገቡ የምግብ፣ የአልባሳትና የቅርጻ ቅርጽ ምርቶችን በቀጥታ ስለሚሸምቱ የኢንዱስትሪ ምርቶች በቀጥታ ገበያ ያገኛሉ ብለዋል። ይህም ከአነስተኛ ቢዝነሶች (እንደ ጫማ ማስጠረግና ቡና ማፍላት) ጀምሮ እስከ ውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) መሳብ ድረስ ሰፊ የሸቀጥ ትራንዛክሽንና የኢኮኖሚ ትስስር እንደሚፈጠር አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሌላኛውና ዋነኛው የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዓላማ የሀገሪቱን ገጽታ መቀየር መሆኑን አስምረውበታል።

” እንደ ኢትዮጵያ ያለ ድንቅ፣ ታሪካዊ ፣ ምርጥ ሀገር ስሟ ጠልሽቶ፣ ስሟ ጠፍቶ በችግር በረሃብ ብቻ እንድትታወቅ በከፍተኛ ደረጃ እንደተሰራባት ” ተናግረዋል።

” ይሄን የሰሩትባት በግምት አይደለም ፤ ረሃብ እኛ ጋር ብቻ ስለሆነ አይደለም ፤ የረሃብ ምልክትና ስያሜ መዝገበ ቃላት ላይ የገባው ኢትዮጵያ ብቻ ችግር ስላለ አይደለም ” ያሉት ጠቅላይ ሚስትሩ ፥ ” ‘ አፍሪካ ውስጥ ያልተገዛች ሀገር ኢትዮጵያ ስለሆነች አለመገዛቷ ይበልጥ እንድትጎዳ አድርጓታል ፤ እኛ ያላሠለጠነው፣ እኛ ያልገዛነው፣ እኛ ያልመራነው አይለማም፣ አይሰማም፣ አይበለጽግም ‘ የሚለውን ናሬሽን (Narration) ለማስረፅ እንዲመቻቸው ነው ” ብለዋል።

” የኢትዮጵያን ውድቀት አጉልቶ የሚናገሩበት ዋነኛው ምክንያት ‘ ከገዛናቸው ያልገዛናት በከፋ ሁኔታ ላይ ነች ‘ እና ‘ መገዛትን ተቀበሉ ‘ የሚል እሳቤ ያላቸው ሰዎች ጭምር አስበው የሰሩበት ጭምር ነው ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ቱሪስቶች መጥተው ሀገሪቱን ሲያዩ ይህ የተሳሳተ ትርክት እንደሚቀየርና ይህም ትልቅ ድል መሆኑን አስገንዝበዋል።

@tikvahethiopia

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ዜጋዬ ተገድሏል ያለችው ጋና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ገባች

አንድ ጋናዊ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ካለው ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ...

«የማይናገረው ልዑል» መጽሐፍ በታላቅ ድምቀት ሊመረቅ ነው

ደራሲ መሠረት ክንፈ ኃይሌ ከኦቲዝም ጋር ከሚኖረው ልጇ ልዑል...

በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር የሚደረግ ንግድ በገንዘብ መጠን ተገደበ

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር የሚከናወነውን...

(IMF) ከ460 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር አፀደቀ

አዳዲስ ብድር በመውሰድ ረገድ ጥንቃቄ እንድታደርግ ኢትዮጵያን ያስጠነቀቀው IMF...