በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ባለፈው ሰኞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አባላት አቶ አበበ አካሉ እና አቶ ይስሀቅ ወልዳይ እንዲሁም የፓርቲው ጠበቃ አቶ አበራ ንጉስ ላይ ፍርድ ቤት የ12 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ፣ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።
ችሎቱ ለዛሬ ቀጥሮ ተጠርጣሪዎች ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ነበር። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ከማስተላለፉ አስቀድሞ፤ ፖሊስ በጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻው ያካተተውን እና ተጠርጣሪዎች ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጋር ያደረጓቸውን ቃለ ምልልሶች ሊንኮች በትላንትናው ዕለት እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
የፌደራል ፖሊስ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ተጠርጣሪዎቹ “የብሔር እና የሃይማኖት ግጭትን ለመፍጠር በማሰብ በውጭ ሀገር በሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጩ ነበር” የሚል ውንጀላ አቅርቦ ነበር። ከመገናኛ ብዙሃኑ መካከል በፖሊስ ማመልከቻ ላይ በስም የተጠቀሱት አንከር ሚዲያ፣ ኢትዮ ፎረም እና ኢትዮ 360 መገናኛ ብዙሃን ናቸው።
ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት፤ ፖሊስ ሊንኮቹን ለችሎቱ ማቅረቡን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ተጠርጣሪዎቹ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጋር አድርገዋቸዋል የተባሉትን ቃለ ምልልሶች ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ ንግግሮቹ በሽብር ወንጀል ለመጠርጠር “መነሻ ይሆናሉ” ማለቱን አቶ ሰለሞን አስረድተዋል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ ይህን ሲያብራሩ “ይህ ማለት ግን የቀረቡት ማስረጃዎች ሙሉ በሙሉ [ተጠርጣሪዎቹን] ‘በሽብር ወንጀል ያስጠይቃቸዋል’ የሚል ድምዳሜ ላይ ችሎቱ ደርሷል ማለት አይደለም” ብለዋል። ይልቁንም ተጠርጣሪዎቹ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ያደረጓቸው ቃለ ምልልሶች፤ ፖሊስ ላቀረበው የሽብር ወንጀል ጥርጣሬ መነሻ የሚሆኑ ምልክቶችን የያዙ መሆናቸውን ችሎቱ የተገነዘበ መሆኑ የገለጸበት ነው ብለዋል።
በዛሬው የችሎት ውሎ ተጠርጣሪዎቹ “ቃለ ምልልስ ያደረግነው ዩቲዩብ ላይ በመሆኑ እና የፎረንሲክ ማስረጃው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት እጅ ስለሚገኝ ክስ መመስረት ይቻላል። ስለዚህ ተጨማሪ ምርመራ አያስፈልግም” የሚል መከራከሪያ ማቅረባቸውን ጠበቃቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፖሊስ በበኩሉ ተጨማሪ የሰው ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በማስረዳት፤ ፍርድ ቤቱ የጠየቀውን 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቅድለት ጠይቋል።

የፖሊስን ጥያቄ የተቀበለው ችሎቱ፤ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ከቀረቡበት ጊዜ አንስቶ የሚታሰብ የ12 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ለነሐሴ 11፤ 2018 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። አጭር ጊዜ የፈጀውን የዛሬውን የፍርድ ቤት ሂደት ለመከታተል የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ በቦታው ቢገኝም፣ ወደ ችሎቱ ገብቶ እንዲዘግብ አልተፈቀደለትም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
