አሜሪካ የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ እንዳይገኙ አገደች። አሜሪካ ከፕሬዝዳንት መህሙድ አባስ በተጨማሪ 80 የሚሆኑ ባለስልጣናት በመጪው መስከረም በኒውዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ አመታዊ ጉባኤ ላይ እንዳይሳተፉ ማገዷ ተነግሯል። ይህ የአሜሪካ እርምጃም ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረትን ፈጥሯል ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የፍልስጤም አስተዳደር እና የፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት አባላት ቪዛ መሰረዙን አስታውቀዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ውሳኔው ለአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ሲባል የተወሰደ መሆኑን አመላክቷል ። እንዲሁም የፍልስጤም አስተዳደር የሰላም ስምምነቶችን ጥሷል ፣ ሽብርተኝነትን ያበረታታል ” ሲልም ከሷል።
የፍልስጤም አስተዳደር የአሜሪካ ውሳኔ ያወገዘ ሲሆን ዓለም አቀፍ ህግን የሚጥስ ብሎም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስምምነት ህግን የሚቃረን ነው ብሏል። አሜሪካም ውሳኔዋን እንድትቀይር አሳስቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ ሁሉም አባል ሀገራትና ቋሚ ታዛቢዎች በተመድ ጉባኤ ላይ እንዲወከሉ መፍቀድ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ የአሜሪካን አርምጃ አውግዟል ።
የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ድርጅቱ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል ።
በ1947ቱ የተመድ ስምምነት መሰረት አሜሪካ በአጠቃላይ የውጭ ዲፕሎማቶች በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ ቪዛ መስጠት ይጠበቅበታል።
ዘገባው የስካይ ኒውስ
