በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ግጭትና ጥቃቶችን ሸሽተዉ ደቡብ ወሎ ዉስጥ የሠፈሩ ተፈናቃዮች በረሐብ እየተሰቃዩ መሆኑን አስታወቁ።
የደሴዉ ወኪላችን ኢሳያስ ገላዉ ያነጋገራቸዉ ተፈናቃዮች እንዳሉት ባለፈዉ ግንቦት ወር የመጨረሻዉን የርዳታ እሕል ከታደሉ ወዲሕ ርዳታ አግኝተዉ አያዉቁም።ተፈናቃዮቹ እስከ ግንቦት ድረስ በነብስ ወከፍ 15 ኪሎ ግራም በቆሎ ይታደላቸዉ እንደነበር ተናግረዋል።
ባለፉት 3 ተከታታይ ወራት ግን እርዳታ ባለማግኘታቸዉ ረሐብ ሥለጠናባቸዉ ለልመና በየከተማዉ እየተንከራተቱ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።
አንዳድ አካባቢ ረሐብ፣ በሽታና ተስፋ መቁረጥ የተፈናቃዮችን ሕይወት ማጥፋቸዉ ተዘግቧልም።የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን «ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ» ባለዉ ባካባቢዉ በሚደረገዉ ግጭት ምክንያት ለተፈናቃዮች የምግብ ዕርዳታ ማድረስ አለመቻሉን አስታዉቋል።ደቡብ ወሎ ዞን ዉስጥ 34 ሺሕ ተፈናቃዮች በ11 መጠለያ ጣቢያዎችና ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀይጠዉ ይኖራሉ።
