ዩናይትድ ኪንግደም እና አምስት አገራት በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ የሚደረግ የነዳጅ መርከቦች ጉዞን ደኅንነት ለመጠበቅ “ተገቢ ጥረቶችን” ለማድረግ “ዝግጁ” መሆናቸውን ገለጹ።
ዩናይትድ ኪንግደም እና አጋሮቿ በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢራን በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አውግዘዋል።
በተጨማሪም በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የምትፈጥረውን ስጋት እንድታቆም ጥሪ አቅርበዋል።
“በባሕር ላይ የመቅዘፍ ነፃነት የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርኅ ነው” ሲሉ የዩኬ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣ የኔዘርላንድስ እና የጃፓን መሪዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል።
“የኢራን ድርጊት ውጤት በሁሉም የዓለም ክፍሎች በተለይም በጣም ተጋላጭ የሆኑት እንዲሰማቸው ያደርጋል።”
ቡድኑ በተጨማሪም የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ መተላለፊያ በሆነው የባሕር ወሽመጥ ላይ ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ለማድረግ “ተገቢ ጥረቶችን” ለማድረግ “ዝግጁነቱን” ገልጿል።
አገራቱ አክለውም “በዝግጅት ዕቅድ ላይ የተሳተፉ አገራት ያላቸውን ቁርጠኝነት በደስታ እንቀበላለን” ብለዋል።
ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷን ተከትሎ የዓለም አቀፍ የነዳጅ እና ጋዝ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።
በእስራኤል እና በአሜሪካ ለሚፈጸምባት ጥቃት አጸፋ ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እየፈጸመች ነው።
ይህንንም ተከትሎ ዋና ዋና አገራት በኢራን ላይ የሚካሄደው ጦርነት ያስከተለውን ተጽእኖ ለመግታት በሚል ለድንገተኛ ጊዜ ካስቀመጡት ክምችታቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ለመልቀቅ ተስማምተዋል።
ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የሚደረግ ጉዞን ለመጠበቅ አገራት የባሕር ኃይላቸውን እንዲያዋጡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
BBC
