ነጻነትን ወደ ሕይወት ለመመለስ ጥሯል ። አልተሳካለትም ።
ምክንያቱን ለማወቅ ፍላጎት የለኝም ። አልጠይቅም ። ደግሞም አይነግረኝም ። ሰይፉን የምታውቁት የመሰላችሁ ብዙዎቻችሁ ተሳስታችኋል ። የሚያውቁት ጥቂቶች ይኖራሉ ። ካሁን ቀደምም እንዳልኩት ሰይፉ ፋንታሁን ቀልዱ ቁምነገሩን የሸፈነበት ሰው ነው ። " ቧልተኛ " ነው ሰይፉ ። አንዳንዴ በትልቅ ቁምነገር ሳይቀር ይቧልታል ። " ምን ሆኗል ? "ም እንለዋለን ። ገፋ ሲልም እንጽፍበታለን ። እሱ ይቀጥላል ። ብዙውን ጊዜ ግን ( አልታደልን ይሆናል ) መልካምነቱን አናወራለትም ። ደግሞስ ከየት አምጥተን እናውራለት ? እንደ ሀገር ወግ ልማድ ፣ እንደ ዘመኑ ቋንቋ አይናገር ። ግራው ሲሰጥ ቀኙ አይቀርጽ ። ወይም ደግሞ አድርጎ እሱ እንዳልፈለገ አድርጎ በጎን አይናገር ። ከሁሉም በላይ ሰይፉ የሰው ስቃይ ላይ አይጨፍርም ። ያጣ ሰውን ክብር አይነፍግም ። ሚሊዮን ብርን አሰጥቶም በሰው ላይ አይፎክርም ። እንደ ቀልድ እልፍ ነው የሚለው ። ሰውን መርዳት ላይ በትክክልም የክርስትናን መርህ የሚከተል ነው ። " አንድ ስሜ አይጠቀስ ያለ ወዳጄ ከአሜሪካ ከዳርፉር . . . " የሚለው ብዙውን ጊዜ ውሸቱን ነው ። ራሱ ነው የሚያደርገው ። አንዳንዴ እውነት ይሆናል ። ወደ ዋናው ጉዳይ ልመለስ ።
የዛሬ ዓመት ገደማ ነጻነት ወርቅነህ ታሞ ህንድ ሀገር ሲሄድ ሰይፉ ፋንታሁን 1,000,000:00 ገደማ ( ቢበልጥ እንጂ አያንስም ) ሰጥቷል ። ከጥቂት ወራት በፊትም ኢትዮ አሜሪካዊት ሀኪም ከአሜሪካ አስመጥቶ ( በራሷ መጥታም ይሆናል ) የሚከፈለውን ከፍሎ አሳክሞታል ። " የሚያስፈልግ ወጪ ካለ እኔ አመጣለሁ " ብሎ ነጻነት ራሱን አረጋግቶ ህክምናውን እንዲከታተል ሞክሯል ፤ ነግሯል ፤ ለምኗል ። የነጻነት መጨረሻ ይህ እንዳይሆን ሰይፉ ፋንታሁን ጥሯል ። ሰይፉ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጥቂት ሰዎችም ( " እገሌና እገሌ " የማልላቸው ) ሰዎችም ነጻነት ወደ ሕይወት እንዲመለስ ፣ ለልጆቹ መኖሩ እንዲቀጥል ፣ ሕዝብም እንዲህ እንዳይሰበር ለማድረግ የጣሩ ነበሩ ። እነዚያ ሰዎች ዛሬ በቀብሩ ፊት ላይ የሉም ። እንዳይሆኑ ተከልክለው አይመስለኝም ።
እንዲሆን የፈለጉት ባለመሆኑ ልባቸው ተሰብሮ ይመስለኛል ። ቁጭት ይኖርባቸዋል ፤ ፀፀት ግን ሌሎች ጋ እንጂ እነሱ ጋ የለም ። ሰይፉ ፋንታሁንን ወደ መድረክ አስወጥቶ ያላናገረው ይህ ቁጭት ይመስለኛል ። ልፋቱ መና መቅረቱ ፣ ያሰበው አለመሆኑ ይሆናል ። ወይም ሌላ ይሆናል ። ብቻ ሰይፉ ፋንታሁን ( እና ሌሎች ጥቂት ወዳጆቹ ) ዛሬ የነጻነት ወርቅነህ ቀብር እንዳይሆን የቻለውን ያህል ( ከዚያም አለፍ ብሎ ) አድርጓል ። ባይፀፅተውም ግን ይቆጨዋል ። ያሰቡት ፣ የሞከሩት ሳይሆን ሲቀር ይቆጫል ። ሰይፉም ሊቆጨው ይችላል ። "*እንዲህ ማድረግ ሲገባኝ አላደረኩም " ወይም " ማድረግ ሳይገባኝ አድርጌያለሁ " የማለት ፀፀት ግን አይኖርበትም ። ሌሎች ደግሞ በአንጻሩ ጸጸት ይኖርባቸው ይሆናል ። እሱ ይቆይ ። ወዳጄ ሰይፉ ፋንታሁን ለነጻነት ወርቅነህ አድርገህ ላልተናገርከው ፣ ለሌሎች በምሥጢር ደብቀህ ለምታደርገው ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ ። የተደበቀን የሚገልጥ አምላክ ይይህ ፤ ያወጣኸው ሁሉ በብዙ እጥፍ በዓለም ይመለስ ።
ለመደምደሚያ እንዲሆን ከዚህ ቀደም ብዬ የለጠፍኩትን እዚህ ልድገመው ።
" በነገራችሁ ላይ ፦ በቀብራችሁ ላይ ማቅ ለብሰው ከተገኙት ያልተገኙት ፣ ፀጉራቸውን እየነጩ ካለቀሱት ዝም ያሉት የእናንተ ጠቃሚ የሕይወት ወዳጆች ሊሆኑ ይችላሉ። ችግሩ ግን ሳትረዷቸው አልፋችኋል "
(ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ)
