የሱዳን ብሔራዊ ጦር ለሦስት ዓመታት የተካሔደውን ጦርነት ለማቆም አሜሪካ ያዘጋጀችውን ምክረ-ሐሳብ የሚቀበለው በመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከተቆጣጠራቸው ከተሞች ለቅቆ ሲወጣ እንደሆነ ቅድመ-ሁኔታ አስቀመጠ።
አሜሪካ ያቀረበችውና ሬውተርስ የተመለከተው ምክረ-ሐሳብ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ወዲያውኑ ለ90 ቀናት ተኩስ እንዲያቆሙ እንደሚጠይቅ የዜና ወኪሉ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪ ምክረ ሐሳቡ ግጭቱን በዘላቂነት የሚያቆም የተኩስ አቁም ለማድረግ ድርድር እንዲፈቅዱና ምርጫ እስኪካሔድ ድረስ በሲቪል ፖለቲከኞች የሚመራ ሽግግር እንዲኖር ጥሪ እንደሚያቀርብ የሬውተር ዘገባ ይጠቁማል።
በዚሁ ሰነድ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ታጣቂዎች ከሰሜን ዳርፉርና ከሰሜን ኮርዶፋን በውስኑ ለቀው እንዲቀወጡ የሚጠይቅ ሐሳብ ተካቶበታል። ታጣቂ ቡድኑ ከሁለቱ አካባቢዎች ለቆ ሲወጣ በተባበሩት መንግሥታት የሚመራ ተልዕኮ ድጋፍ እንዲያደርግ ታቅዷል።
በጦሩ የሚመራው የሱዳን መንግሥት በሰነዱ የተካተቱ አብዛኞቹን ምክረ ሐሳቦች ቢቀበልም ታጣቂ ቡድኑ ለቅቆ የሚወጣው በውስኑ መሆኑን ግን እንዳልተቀበለ ሬውተርስ ዘግቧል።
የሱዳን መንግሥት እንዲያውም የመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከሁለት ዓመታት በፊት ከተቆጣጠራቸው ከሁሉም ከተሞች ለቅቆ መውጣት አለበት የሚል አቋም አለው። ይህ አቋም ከዚህ ቀደም ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር የተሞከሩ ጥረቶች እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ስለ ጉዳዩ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም ዩናይትድ ስቴትስ ከሱዳን ብሔራዊ ጦር እና ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ለሰብአዊነት ስለሚደረግ የተኩስ አቁም እና የሰላም ዕቅድ ውይይት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ግን አረጋግጠዋል።
