በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ግንቦት 23 እና 24 ቀን፣ 2018 ዓ.ም. በአከባቢው ደርሶ በነበረው የታጣቂዎች ጥቃት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በርዳታ አቅርቦቶች መቋረጥ መቸገራቸውን ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ተፈናቃዮቹ በጥቃቱ ወቅት በደረሰባቸው የቤት ቃጠሎና የንብረት ውድመት ወደ መኖሪያቸው ቀየያቸው ለመመለስም ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል ፡፡ አከባቢው ላይ አሁንም ከሥጋት የፀዳ የታጣቃዊች እንቅስቃሴ ስለመኖሩም ነዋሪዎቹ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በብዙ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረው በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ግንቦት 23 እና 24 ቀን፣ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በታጣቂዎች ጥቃት ደርሶባቸው በተለይም በስፋት ከጨፋ ቀበሌ የተፈናቀሉት ነዋሪዎች አሁንም ድረስ በአጎራባች ቀበሌያት ተጠልለው እንደሚገኙ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡
“በርካቶች የተፈናቀሉት ጎረቤት ቀበሌያት እሬቻ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን፣ ሱንቴ ቅድስት ማሪያም፣ አሰኮ ወረዳው ላይ እንዲሁም ሪቡ የሚባል ደጋ አከባቢ ነው” ያሉት ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን ያጋሩን አንድ አስተያየት ሰጪ ተፈናቃይ፤ በየአከባቢው ተፈናቅለው ያሉት ተጎጂዎች ቤታቸውም በመቃጠሉ ተመልሰውም ለመቋቋም እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡
ተፈናቅለው የሚገኙት ሌላው አስተያየት ሰጪ፤ “እኔ እዛው ነው ያለሁት፤ አንድ አራት ቀንም ለምን ቤታችሁ ሲቃጠል ተመለከታችሁ በሚል 13 ሰዎች ታስረን ነበር፤ የእኔም የእናቴም ቤት ተቃጥሏ ከህብረተሱ ጋር” በማለት ቤታቸው ሁለት ጊዜ በመቃተሉ በአከባቢው ተመላልሶ በተፈጠረው ጥቃት ተጎጂ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አሁንም ድረስ በአከባቢው ላይ የታጣቂዎች የጥቃት ሙከራዎች ማስተዋላቸውን የገለጹት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ተፈናቃይ፤ ነዋሪዎች በስፋት የተፈናቀሉባቸው አከባቢዎች ላይ አዲስ ጥቃት ባይኖርም የተፈናቀለው ማኅበረሰብ ግን የተለያዩ ችግሮችን እያሳለፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
“ሕዝቡ ተፈናቅሎ ስላለቀ አዲስ ጥቃት የለም፤ ከሰሞኑ ግን ዲቡ የሚባል መሻገሪያ ላይ እያደፈጡ በግንቦት 24 ጥቃት የተቃጠለው የደለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክሰርስቲን አገልጋይ ላይ ጥቃት ሲከፍቱ ሁለት የፀጥታ አካላት አጠገባቸው ስለነበሩ በህይወታቸው ላይ ጉዳት ሳይደርስ ወጥተዋል” ነው ያሉት፡፡
የእሳቸው መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በግንቦት መጨረሻው ጥቃት በርከት ያሉ መንደሮች እንደወደሙ መሆናቸውንም የገለጹት ተፈናቃዩ፤ መንግስት አከባቢውን በማረጋጋት እልባት እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡
ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ እና ክትትል
ለተፈናቃዮቹ ስለሚደረግ ድጋፍ እና ክትትል ጥያቄ ያቀረበላቸው የአርሲ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሶሪ ወጊ በግንቦት 23 እና 24 በታጣቂዎች በደረው ጥቃት ለተፈናቀሉ የአሰኮ ወረዳ ነዋሪች ብርቱ ክትትል ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
“ከ90 በመቶ በላይ ተመልሰዋል፡፡ አሁን መሬት ላይ መሰራት ያለበት ስራ ተሰርቶ ድጋፍም እየተደረገላቸው ነው፡፡ እስከ መጨረሻው ጠንካራ ክትትል እያደረግን ነው፡፡ ችግርም ካለ ወርደን የምናጣራ ነው የሚሆነው” ብለዋል፡፡
የአከባቢው ተፈናቃዮች ግን በርካቶች ወደ ቀዬያቸው ተመልሰዋል በሚለው አስተያየት አይስማሙም፡፡ አንድም በጸጥታ ስጋት ሁለትም የነበራቸው ንብረት ቀዬያቸው በመውደሙ በሚባለው ልክ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው እየተመለሱ አለመሆናቸውን ነው የሚያስረዱት፡፡
“ተፈናቃዮች ገብተዋል ብለው በቴሌቪዥን ሲናገሩ እሰማለሁ፤ ግን አንድም የገባ የለም፤ ያው ቤተክርስቲኑም እንደተዘጋ ነው፡፡ ህዝቡም እንደ ሸሸ ነው፡፡ ደለታ ቅዱስ ገብርኤልም እንደተቃጠለ ነው ያለው፡፡ እርዳታም ቆሟል ህዝቡ በስቃይ ላይ ነው ያለው” ይላሉም፡፡
የአርሲ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ሶሪ ግን፤ “ያው በፊት ከተከሰተው ጥቃት ሌላ አዲስ ጥቃት የለም፤ አሁን እንደሚባለው ብዙዎች ወደ ቀዬያቸው አልተመለሱም፤ የእርዳታ ችግርም አለ የሚለውን መረጃ እኛ የለንም፡፡ እኛ ያለን መረጃ ሁሉም ወደ ቀዬው እንዲመለስ ብርቱ ስራ እየተሰራ መሆኑን ነው” ይላሉ፡፡
የመንግስት የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የ22 ሰዎች ሕይወት አልፏል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባሳለፍነው ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በአርሲ አሰኮ ተከስቶ በነበረው ጥቃት የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች እና ሲቪሎችን አካቶ 11 ሰዎች መሞታቸውንና የተፈናቀሉትን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አከባቢው ላይ የተከሰተውን ጥቃት የሃይማኖት ግጭት አድርጎ ማቅረብ የሚኮነን ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
የአከባቢው ተፈናቃዮች እንደሚሉት፤ “በቅርብ ጊዜው ጥቃት 11 ሰዎች ሲገደሉ አጠቃላይ 2018 ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰተው የአማጺ ታጣቂች ጥቃት የመንግስት የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የ22 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡”
DW
