(መላኩ ብርሃኑ)
አንድ እንደዋዛ ሳናብላላው ያለፈ ፣ ቢያንስ በኔ እይታ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን የከተማው አስተዳደር ውሳኔ አለ፡፡ የ11ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የትምህርት ሰዓት ጭማሪ ጉዳይ፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከሰሞኑ “የ11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል” በሚል ምክንያት በከተማዋ የሚገኙ የግልና የመንግሥት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ ከሰኞ እስከ አርብ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት እንዲማሩ ፣ ጠዋት ደግሞ በአንድ ሰዓት ወደ ትምህትት ቤት እንዲገቡ ፣ በተጨማሪም በተመረጠ ትምህርት ቤት አንድ ላይ ቅዳሜና እሁድ እንዲማሩ የሚያስገድድ መመሪያ አውጥቷል፡፡
እርግጥ ነው…የ12ኛ መልቀቂያ ፈተና ከሚፈተኑ ተማሪዎች መካከል ወደዩኒቨርሲቲ የሚያልፉት እጅግ አናሳ ቁጥር ያላቸው ብቻ መሆናቸው እንደወላጅ እኛን፣ እንደአስተዳዳሪ አካልም መንግስትን ማሳሰቡ ተገቢ ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር እንደባለቤት በየዓመቱ የወደቁ ተማሪዎችን ቁጥር ለወላጅ ከማርዳት በተሻለ ለዚህ አሳሳቢ ችግር መፍትሄ ማፈላለግ ግዴታው ነበር፡፡በዚህ ዙሪያ ምን እየሰራ እንደሆነ እኔ አልሰማሁም፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ግን ከሰሞኑ ይህንን ‘የመውደቅ ምጣኔ’ ‘በማለፍ ምጣኔ’ ለመቀየር ብሎ ያወጣውን አስገዳጅ መመሪያ ሰምቻለሁ፡፡ በግሌ ይህ ውሳኔ የተጠና እና ሳይንሳዊ ነው ብዬ አላምንም፡፡
በራሴ ቤት ትዝብት ልጀምር፡፡ ናኒዬ ዘንድሮ 10ኛ ክፍል ናት፡፡ ትምህርት ከተጀመረ ቀን አንስቶ ከኛ ጋር ቁጭ ብላ ለማውራት ደቂቃ ጊዜ እንኳን የላትም፡፡ ከትምህርት ቤት መጣች ፣ ጥቂት እረፍት አድርጋ ሃይል ሰበሰበች …ከዚያ ክፍሏ ገብታ እስከእኩለ ሌሊት ከትምህርት ቤትና ከኦንላይን ምንጮች ጋር ትንቅንቅ ላይ ናት፡፡ ጥናትና የቤት ስራ ብቻ ሳይሆን ያልገቧትን ሃሳቦች ማብራሪያ ፍለጋ ኦንላይን ምንጮችን ስታስስ ታመሻለች፡፡ በቀን ያለማጋነን ከ13 ሰዓት በላይ ትምህርት ላይ ነው የምታሳልፈው፡፡
እኔ በበኩሌ ራስን እረፍት በመንሳት የማጥናትና መማር ሂደትን ብዙም ባልደግፍም ከምትማራቸው ትምህርቶች ብዛት፣ በላይ በላይ ከሚሰጡ አሳይመንቶችና ከሚላኩት ፓወርፖይንቶች ብዛት፣ በአንድ ሳብጀክት ብቻ በየቀኑ ከሚሸፍኑት ፖርሽን ብዛት፣ ጠለቅ ብላ ለመረዳት ከምታስሳቸው ኦንላይን ምንጮች ብዛት ወዘተ አንጻር ሳየው “እንዲህም ሆና ቀኑ በበቃትና ጫናውን ተቋቁማ ከዘለቀች ጥሩ ነው” ብዬ ማለፍ ግድ ሆኖብኛል፡፡ የናኒ ጥቂት እረፍት ቅዳሜና እሁድ ከሰዓት ሰንበት ትምህርት ቤት ለመሄድ ከደብተሯ የምትለያይበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ዓላማዋ ሩቅ ስለሆነ ዛሬ በልጅ ጉልበቷ አቅሙን ከሰጣት ‘ እንግዲህ ትቻለው’ ብዬ ትቻታለሁ፡፡
ናኒ እንደምትነግረኝ ከሆነ አሁን አሁን በትምህርት ቤት መምህራን ከሚሰጣቸው ትምህርት በላይ ከመጽሃፍትና ኦንላይን በሚገኙ አጋዠ ግብዓቶች በንባብ የሚገኘው ዕውቀት ጥልቅ እና የበለጠ ደጋፊ ነው፡፡ “መምህራኖቻችን መሰረታዊውን ጉዳይ ብቻ ያስጨብጡናል፣ እኛ ደግሞ ከዚህም ከዚያም ፈላልገን በርዕሰጉዳዩ ላይ አንብበንና ሰርተን እውቀታችንን እናሰፋለን’ ነው ያለችኝ፡፡ ከ2 ዓመት በኋላ ለሚጠብቃት ፈተና ራሷን እያዘጋጀችበት ያለችበት መንገድም ይኼው ነው፡፡ አዲሱ ውሳኔ ግን ገና ከአሁኑ ውጤታማነቷ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር በጣም አስግቷታል፡፡
አስተዳደሩ ተማሪዎች ከሚማሩበት ጊዜ ይልቅ የሚያርፉበት ጊዜ የበለጠ መስሎት በተገበረው አዲስ መመሪያ መሰረት ግን ናኒ ከሚቀጥለው አመት በኋላ ከሰኞ እስከሰኞ ከአዳር በመለስ ውሎዋ ሁሉ ትምህርት ቤት ሊሆን ነው፡፡
በነበረው አሰራርና መምህራንና ተማሪዎች በተስማሙበት አካሄድ የክፍል ትምህርት አማራጭ ምንጮች ተጨምረውበት ካልተነበበ በመምህራን ገለጻ ብቻ የማይገፋ ነው፡፡ አሁን ግን ተመልሶ ወደክፍል ጥገኝነትና ሁሉንም ነገር በመምህራን ትከሻ ላይ ወደመጣል ሊሸጋገር ነው፡፡ ያ ደግሞ በአንጻራዊነት ሲታይ ተማሪዎች ከአንድ ከተቀነበበ ከባቢ ወጥተው ጥቂት እያረፉም ብዙ እየሰሩም የሚያካሂዱትን የቤት ውስጥና የላይብረሪ ጥናት ጊዜያቸውን ሙሉ በሙሉ ይበላባቸዋል፡፡
ትምህርት በተፈጥሮው የተጠና የእረፍት ጊዜ ከሌለው በጣም አሰልቺ ሂደት ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከክፍል ትምህርት ባለፈ extracurricular activities የሚደረጉት ይህንን መሰልቸት ለማስቀረትም ጭምር ነው፡፡ የሰው ልጅ አንድን ነገር ምን ቢወደው በተመሳሳይ ሁኔታ ሲያገኘው ይሰለቸዋል፣ ይጠላዋል፡፡ ይህ ተፈጥሮ ነው፡፡
ተማሪዎች በቀን የተወሰነ ሰዓት፣ በሳምንትም እንዲሁ ተሰልቶ ሰፋ ላለ ሰዓታት እረፍት ቢያደርጉ ይመከራል፡፡ ለግል ንጽህና መጠበቂያ ፣ ለሃይማኖታዊ ስርዓት መከታተያ፣ ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ለመውሰጃ እና ለመወያያ የሚሆን ጊዜ በጣም ያስፈልጋቸዋል፡፡ School- Life Balance መተግበር ካልቻሉ Burnout ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ እንኳን የታቀደውን ውጤት ሊያመጣ ጭራሽ ብዙ ተማሪዎችን ከመስመር ሊያስወጣና ወዳልተፈለገ ጭንቀት፣ መንሸራተት እና ማፈግፈግ ሊመራ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ብዙ የትምህርት ባለሙያዎችም እየተናገሩ ያሉት ይህንን ነው፡፡
ለመሆኑ ይህ ውሳኔ ምን አይነት ጥናት ተደርጎበትና በምን መልክ አዋጪ ይሆናል ተብሎ ነው ተግባራዊ እንዲደረግ የታዘዘው? ምን ያህልስ ሳይንሳዊ ነው?
ከኛ በእጅጉ የራቀው የሰለጠነው አለም ውጤት ለማምጣት የትምህርትና ጥናት ጊዜን ማርዘም ሳይሆን አጭር ግን ደግሞ በጣም ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀምን ይመክራል፣ የትምህርት አመራሩም በዚሁ መንገድ የተቃኘ ነው፡፡
ቻይና እኮ ከዘንድሮ ጀምሮ በወሰደችው እርምጃ እስከ12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በግዴታ ክፍል ውስጥ የተወሰነ ጊዜ እንቅልፍ እንዲተኙ አዝዛለች፡፡ ሲታጠፍ ወንበር፣ ሲዘረጋ አልጋ የሚሆን አዲስ ሞዴል የተማሪዎች ወንበር በሁሉም ግዛቶች ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ አንዲሆን አድርጋለች፡፡ ጥቂት ‘ናፕ’ ማድረግ ዐዕምሮን ያድሳል፣ ውጤታማ ያደርጋል ብላለች፡፡ ዝም ብላ አይደለም፣ ሰፊ ጥናት ተደርጎ የተደረሰበት መደምደሚያ ነው፡፡
እኛ ሃገር ምን አዲስ ነገር ተዘጋጀ? ምንም፡፡ ሰዓትና ቀን ግን ተጨመረ፡፡ በዚያ ጀርባና መቀመጫ በሚቆረቁር ዴስክ ላይ ለሰዓታት ተቀምጦ መዋል የሚፈጥረው የራሱ የጤና ችግር እንዳለ ሆኖ መምህራንስ በሳምንት ከ40 ሰዓት በላይ በማስተማር አይደክሙም ወይ? ተማረዎችስ ቢሆኑ ምን ትምህርት ቢወዱ በሂደቱ መሰልቸት ውስጥ አይገቡም ወይ? ክፍል ውስጥ ታፍኖ እያንቀላፉና እያዛጉ መማር ምን ረብ ሊያስገኝ ነው? አስተዳደሩስ ቢሆን ለምን የዚህን አዲስ ውሳኔ Rationale በይፋ አይነግረንም? ትምህርት በግድ ስለተቀጠቀጠ ውጤት ይመጣል ብሎ ማሰብ መነሻው ምን ይሆን?
በእውነት ለመናገር ይህ ጉዳይ እንደወላጅ እጅግ በጣም አሳስቦኛል፡፡ ብዙ ወላጆች ተቃውመውታል የተባለውን ይህንን አካሄድ ‘ኦልሬዲ የተወሰነ ነገር ነው፣ ለናንተ ለማሳወቅ እንጂ የሚቀየር ነገር የለም’ ብሎ ወደትግበራ መግባት የጤና ነው? ለመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ግን ይህንን ያውቃል? ይደግፋል? እናንተስ ልክ ነው ትላላችሁ? መገናኛ ብዙሃንስ ምነው ዝም አላችሁ? ምንም አልገባችሁም ማለት ነው?
እንደወላጅም፣ እንደባለሙያም በጉዳዩ ላይ ሃሳብ እንለዋዋጥ እስኪ፡፡
Education should not become a burden for children at all !! Pressure from teachers and the sheer volume of homework, including holiday classes and assignments, can detract from learning and lead to stress and burnout, making education feel like a chore instead of a privilege.
