ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በዶክተር ጌታቸው ተድላ አበበ የተጻፉ 2 መጽሐፍት ይመረቃሉ፡፡ በዓለም ሲኒማ ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ በሚደረገው የምረቃ መርሀ- ግብር ልዩ ልዩ እንግዶች ይታደማሉ።
የመጀመሪያው መጽሐፍ የወይዘሮ “አበበች” ቶላ ሲሆን፣ ይህች በጎ አድራጊ ሴት በየቀኑ ከ60 እስከ 80 የሚደርሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች ትመግባለች፡፡ የምትመግበውም ልዩ ልዩ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየተዘዋወረች ነው፡፡
ዝክር በሚሆንበት ወቅት፣ ከ100 እስከ 200 ሰዎችን ታበላለች፡፡ በሽተኞችን ከየጎዳናውና ከየጎጆው እያነሳች ሐኪም ቤት በመውሰድ ታሳክማቸዋለች፡፡ የጎዳና ኑሮ አስመርሯቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ የሚፈልጉትን አጥባና አልብሳ፣ የኪስ ገንዘብ ሰጥታ በአውቶቡስ ወደየመጡበት ክፍለ ሀገር ትሸኛቸዋለች፡፡
የእዚህች በጎ አድራጊ ሴት ታሪክ ታፍኖ እንዳይቀር፣ ደራሲ ዶክተር ጌታቸው ተድላ መነበብ ያለበትን የሕይወቷን ታሪክ ዘክረውልናል፡፡
ይህን መፅሐፍ ከዶክተር ጌታቸው ተድላ ጋር በመሆን ያዘጋጀችው ጋዜጠኛ ቤርሳቤህ ጌቴ ስትሆን እርሷም ከዚህ ቀደም 4 መፅሐፍትን ለአንባቢያን ያቀረበች ናት።
በጋዜጠኝነት ላለፉት 14 ዓመታት ያገለገለችው ቤርሳቤህ ጌቴ የቴሌቪዥን ፣የሬድዮ ፕሮዳክሽን እንዲሁም መፅሔቶች በማዘጋጀት የምትታወቅ ባለሙያ ነች።
ሁለተኛው መጽሐፍ – “እጅ የማትሰጥ ነፍስ” ተብሎ የተሰየመ ግለ- ታሪክ ሲሆን፣ አንድ ወጣት በደርግ ዘመነ መንግሥት፣ ከ11ኛ ክፍል ታፍሶ የብሔራዊ ውትድርና ምልምል ሆኖ ወደ ደዴሳ ተወሰደ፡፡
ሦስት ዓመት ሠልጥኖ ሊመረቅና ሊሠናበት ሲደርስ፣ ወደ ጦርነት እንደሚላኩ ሲነገር፣ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ጠፍተው በእግራቸው አዲስ አበባ መመለሳቸውን ያወሳል፡፡ እዚያም ያልተስማማው ወጣት በሚያስገርምና በማያዳፍር ሁኔታ ወደ አሜሪካን መጓዙን ያወጋል፡፡
አሜሪካን ሀገርም እንዳሰበው ሳይሆን ብዙ ጭንቀት፣ ብዙ ጊዜ ዘብጥያ መውረድ አጋጥሞት፣ ያንን ሁሉ ትግል፣ ያንን ሁሉ ጭንቀት እጅ አልሰጥም ብሎ እንዳመጣጡ አሳልፎ፣ ከፍተኛ ከሚባል ኑሮ እንደደረሰ ዶክተር ጌታቸው ተድላ ይህንን ልብ አንጠልጣይ ታሪክ አውግተውናል፡፡
ይህን መፅሐፍ ከዶክተር ጌታቸው ተድላ ጋር በመሆን ያዘጋጀው ታምሩ ጎንቼ ቢልልኝ ሲሆን ባለፉት 30 ዓመታት በሥነ-ፅሑፍ እና በሚድያ ሥራ ላይ ያሳለፈ ነው።
የመፅሀፉ ዋና ደራሲና አሳታሚ በመሆን ትልቁን ሚና የተጫወቱት ዶክተር ጌታቸው ተድላ አበበ ባለፉት 18 ዓመታት ከ 17 በላይ መፅሐፍትን አዘጋጅተው ለህትመት ያበቁ ሲሆን በሙያም የግብርና ኢኮኖሚስትና ደራሲ ናቸው።
ለረጅም ዓመታት በስዊድን አገር የኖሩት ዶክተር ጌታቸው ተድላ ከ2000 ሚሊኒየም በኃላ ሙሉ ጊዜያቸውን ለድርሰት ሥራ በመስጠት ፣የራሳቸውንም ግለ-ታሪክ በሁለት መፅሐፍ ማስነበብ የቻሉ ሰው ናቸው።
ቅዳሜ መፅሐፎቹ ሲመረቁ የባለታሪኮቹ ቤተሰቦች እና ተጋባዥ እንግዶች እንደሚታደሙ ለማወቅ ተችሏል።
