የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በሕገወጥ ተግባራት ላይ የተሳተፉ 310 የምግብ ተቋማት መታገዳቸውን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈፃፀም አስመልክቶ መገለጫ ሰጥቷል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት በምግብ፣ በመድኃኒት፣ በሕክምና መሣሪያዎች፣ በመዋቢያ፣ በትምባሆና በአልኮል ምርቶች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር አድርጓል።
ከክልሎች ጋር በመሆን ባካሄደው የቁጥጥር ስራ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችሏል ብለዋል፡፡
የህብረተሰብ ጤና ለመጠበቅ ባካሄው የቁጥጥር ስራ በተለይ በምግብ ዘርፍ በቁጥጥር ወቅት የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራትን ማግኘት መቻሉን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ግኝቶችን መሰረት በማድረግ የተለያዩ ርምጃዎች መውሰዳቸውን አሳውቀዋል፡፡
ከህገ ወጥ ተግባራቱ መካከልም፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸዉ ባለፈበት ጥሬ ዕቃ ምርት ማምረትና ባዕድ ነገር መጠቀም፣ ምርት ግብአትን በአግባቡ አለመያዝ፣ በነፍሳት የተበላ፣ የተበላሸ ግብአት በማምረቻ ተቋማት መገኘት፣ በደረጃ መሰረት የተሟላ ገላጭ ፅሁፍ የሌላቸዉ ምርቶች ማምረት፣ የተከለከለ ጥሬ እቃ ተጠቅሞ ምርት ማማረት እና እንደ ግብአት ያልተጠቀሙትን ግብአት ምርቱ እንዳለዉ አድርጎ በምርት ገላጭ ፅሁፍ ላይ መፃፍ እንደሚገኙበት አብራርተዋል፡፡
በመሰልና ሌሎችም ህገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው በተገኙ የምግብ አምራቾች፣ አስመጪዎች እና አከፋፋዮች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደተወሰደ ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ‹‹285 የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 384 ስረዛ፣ 39 እሸጋ እና 310 የሚሆኑት ላይ የእገዳ ርምጃዎች ተወስዷልም›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚያደርገውን ቁጥጥር በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስገነዘቡት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ህብረተሰቡም ህገ ወጥ ተግባራትን ሲመለከት ለተቋሙም ሆነ በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ መስጠቱን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ጋዜጣ_ፕላስ
