በቤት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ቀላል ማሽኖችን እና የኢንዱስትሪ ማሽኖችን በአግባቡ ባለመገልገል ምክንያት በቀን እስከ 4 ሰው ጉዳት እንደሚደርስበት የካቲት 12 ሆስፒታል አስታውቋል፡፡
የሆስፒታሉ የፕላስቲክ እና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ጌታው ዓለም፤ በቤት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ስጋና ሽንኩርት መፍጫ፣ ቡና ማፍያ ያሉ ሌሎች ማሽኖችን አጠቃቀም ባለማወቅ ምክንያት በርካታ ሰዎች ለአደጋ እየተጋለጡ እንደሆነ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞችም በማሽን የአጠቃቀም ዕውቀት ማነስ ምክንያት ለአደጋ እንደሚጋለጡ ዶ/ር ጌታው አንስተዋል፡፡
በቂ ልምድ የሌላቸው ሰዎች ወደ ሥራ መሰማራታቸው፣ በቂ የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎች አለመሟላታቸው፣ ከሥራ ለመውጣት በሚደረግ ጥድፊያ እና ተያያዥ ነገሮች አደጋው ለመፈጠሩ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
“አለርት ሆስፒታልን ጨምሮ በሌሎችም የሕክምና ተቋማት እርዳታ ለማግኘት የሚመጡት ተጎጂዎች ቁጥር በቀን እስከ 4 ይደርሳል” ያሉም ሲሆን፤ “ለከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ተዳርገዋል” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ጌታቸው በተጨማሪም፤ የአደጋ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ፣ የአጠቃቀም መመሪያ ወይም ማንዋሎችን በሚገባ በማንበብ አደጋዎችን መቀነስ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
የተጎጂዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የማሽን አጠቃቀም ጉዳይ ላይ ትኩረት በመስጠት የመከላከል ሥራው ላይ አጽንኦት ሰጥተውበታ፡፡
(አሐዱ ሬድዮ)
