የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት በሱዳን ላይ 4ተኛ ዙር ማእቀብ መጣሉን አስታወቀ፡፡ ምክር ቤቱ ዛሬ ባከናወነው ስብሰባው ማእቀብ የጣለው በሁለት ግለሰቦችና ሁለት ተቋማት ላይ ነው፡፡
‹‹በሱዳን ውስጥ ከተፈጠረው የሰብአዊ መብት ጥሰትና ከአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት መደፍር ጋር በተያያዘ›› በሚል ማእቀብ የተጣለባቸው ሁለት ተቋማት አልካላጂ ባንክና ሬድ ሮክ ማእድን ኩባንያ ናቸው፡፡
የአውሮፓ ህብረት እንዳለው አልካላጂ ባንክ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ዋና አዛዥ ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ቤተሰቦች ሰፊ የባለቤትነት ድርሻ የያዙበት ሲሆን በጦርነቱ ወቅትም ለፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ እንቅስቃሴ ወሳኝ የፋይናንስ ምንጭ ነው፡፡
ሬድ ሮክ ማእድን ኩባንያ ደግሞ ለሱዳን ጦር ሀይል ጦር መሳሪያዎችንና ተሸከርካሪዎችን በማምረት ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድቷል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ዛሬ ማእቀብ የጣለባቸው ግለሰቦች ደግሞ አቡ አቅላ መሀመድና ሁሴን ባርሻም ናቸው፡፡
አቡ አቅላ መሀመድ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ኮማንደር የነበሩ ሲሆን ከድተው የመንግስትን ጦር ሀይል የተቀላቀለሉ ሲሆኑ ሁሴን ባርሻም ደግሞ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ወታደራዊ መሪ ናቸው፡፡
እነዚህ ግለሰቦች በአውሮፓ የሚገኝ ገንዘባቸው እንዳይንቀሳቀስ የተደረገ ከመሆኑም በላይ የቪዛ ማእቀብ እንደተጣለባቸውም ምክር ቤቱ አስረድቷል፡፡ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ከሱዳን ጦርነት ጋር በተገናኘ 3 ጊዜ ማእቀቦችን መጣሉ የሚታወስ ነው፡፡
(ዘ-ሐበሻ ዜና)
