በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም ዞን ጅጋ ንዑስ ወረዳ በተለምዶ ለዛ ወንዝ ከተባለው ስፍራ ትናንት እሁድ ነሐሴ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች የ11 ሰው ህይወት ሲያልፍ 17 ሰዎት ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን የአማራ ክልል ፖሊስ አስታወቀ።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ አደጋው የደረሰው 19 ተሳፋሪዎችን ጭኖ ከደብረብርሀን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲጓዝ የነበረ በተለምዶ ሀይሩፍ በሚል የሚታወቀው አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር በልኬ ይርጋ ፍጥነት ላይ የነበረው ተሽከርካሪ ጨኪ ቀበሌ ልቼ ጎጥ አካባቢ ጎማ ፈንድቶበት ሊገለበጥ ችሏል ሲሉ ጠቁመዋል።በዚህም የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አስር ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም ሰባት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክተዋል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጅጋ ንዑስ ወረዳ በተለምዶ ለዛ ወንዝ ከተባለው ስፍራ ከፍኖተ ሰላም ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ የነበረ ተሳቢ የጭነት መኪና ከባጃጅ ጋር ተጋጭቶ ባጃጅ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ ሰባት ሰዎች እና ሁለት እግረኞች በድምሩ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አልፏል ተብሏል።
