በአማራ ክልል የሚገኙ ሆቴሎች ከ2012 ጀምሮ ምንም አይነት የደረጃ ምደባ እንዳልተደረገላቸው የክልሉ የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ለአሐዱ ገልጿል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አባይ መንግስቴ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ በአማራ ክልል የሚገኙ ሆቴሎች ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ይፋዊ ደረጃን አላገኙም።
ምክትል ኃላፊው በክልሉ የመጨረሻው የሆቴል ደረጃ ምደባ የተደረገው በ2012 መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ተቋርጦ የነበረበት ዋና ምክንያት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆኖም ምደባው ይሰጥ የነበረው “የደረጃ አሰጣጥ ስርዓቱ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባወጣው ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ላይ ተመሰረቶ ነው” ሲሉም አቶ አባይ አብራርተዋል።
“እነዚህን መመዘኛዎች ለማሟላት ሆቴሎች የእድሳት እና የማስፋፊያ ሥራዎችን ማከናወን ያለባቸ ሲሆን፤ በCOVID-19 ወረርሽኝና ባሉ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የሆቴል ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ወረርሽኙም ሆነ ክልላዊ ግጭቶች የሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማስተጓጎሉ በቀጣይ የሆቴል ኦፕሬተሮች ለግምገማ አስፈላጊ የሆኑትን መስፈርቶች እንዲያሟሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
የክልሉ የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ችግሮች ቢያጋጥሙትም በአሁኑ ወቅት የሆቴል ደረጃ አሰጣጥን ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ክልሉ ቀስ በቀስ እየተረጋጋ ባለበት በአሁኑ ወቅት የሆቴሎችን ሁኔታ ለመገምገም እና ዘርፉን ለመደገፍ እየተሰራ ነው ብለዋል።
