በኢትዮጵያ በስደትና ጤና ላይ የተደረጉ የምርምር ጥናቶች አነስተኛ በመሆናቸው ከፍልሰት ጋር የተገናኙ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ክፍተት እንደሚፈጥር ተጠቁሟል። የኢትዮጵያዊያን ስደተኛ የቤት ሰራተኞችን ጤና እና ደህንነት ለማሻሻል ያለመ ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡
INNOVETH የተሰኘው የዚህ ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ካሳሁን ሃብታሙ እንደተናገሩት ወደ ተለያዩ የአረብ ሀገራት ለስራ የሚያቀኑ ሴት ኢትዮጵያዊያን በርካታ ችግሮች ያጋጥማቸዋል።
የቋንቋ፣የባህል ተፅእኖ፣የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ለስነ አእምሮ እና ለስነተዋልዶ ጤና ችግሮች እንደሚዳረጉ ጠቁመዋል።
እንዲህ ያለ ችግር የሚያጋጥማቸው ሴቶች በቂ የሆነ የጤና አገልግሎትን እንደማያገኙ አስተባባሪው ገልፀው ይህን ክፍተት ለመሙላት እንዲቻል ፕሮጀክቱ ይፋ ሆኗል።
ፕሮጀክቱ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኛ የቤት ሰራተኞችን ጤና እና ደህንነት በቴክኖሎጂ ፈጠራ በመታገዝ ለማሻሻል ያለመ መሆኑን ዶክተር ካሳሁን ጨምረው ተናግረዋል።
የሞባይል አፕልኬሽንን በመጠቀም እና የባለሙያዎችን ቡድን ባካተተ መልኩ ስደተኞች ባሉበት ቦታ መረጃ ማግኘት የሚችሉበት እድል ተመቻችቶላቸዋል።
የሚገጥማቸውን የጤና ችግሮች በተለይም የስነ አእምሮና የስነልቦና ጉዳቶችን ማሻሻል እንዲችሉ የሚያስችላቸውን መረጃ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ተብሏል።በተጨማሪም ወደ አረብ ሀገራት ጉዞ ከመጀመራቸው አስቀድሞ አስፈላጊውን ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል ሲሉ አሰተባባሪው ገልፀዋል።
ብስራት ራዲዮ
