ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላትን ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጥ የመጀመሪያው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) ዩኒቨርሲቲ ሊገነባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ታላቅ የምርምርና የትምህርት ተቋም ግንባታ ይፋ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ነው።
ይህ አዲስ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የታመነ ሲሆን በተለይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በዳታ ሳይንስ እና በሮቦቲክስ ዘርፎች የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ታቅዶ የተቀረጸ ነው።
ለእያንዳንዱ የአፍሪካ ሃገር ሁለት -ሁለት ስኮላርሽፕ እንሰጣለን ብለዋል።
ስራዎቻችን በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እናጠናቅቃለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መሆኑ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላትን ተሳትፎ ለማሳደግ የጀመረችው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው መገንባት ለኢትዮጵያ ወጣቶች አዳዲስ የፈጠራ እድሎችን ከመፍጠሩም በላይ ሀገሪቱን በቀጠናው ቀዳሚ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥነዋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ እንዲህ ያሉ ልዩ የትኩረት መስኮች ያላቸው የትምህርት ተቋማት መገንባታቸው ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ Fourth Industrial Revolution ውስጥ ያላትን ድርሻ ከፍ የሚያደርግ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ስራ ሲጀምር የምርምር ስራዎችን ከማከናወን ባለፈ ለተለያዩ የልማት ዘርፎች የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን በማፍለቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
