በስኮትላንድና በአሜሪካ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች በዓለም ለመጀመሪያ ግዜ በሮቦት የታገዘ የስትሮክ ቀዶ ህክምና ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ቀዶ ህክምናውን የስኮትላንድ ዱንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር እሪስ ግራንዋልድ እና በአሜርካ ፍሎሪዳ የሚገኙት ዶ/ር ሪቻርድ ሀኔል በሮቦት ማሽን በመታገዝ ማከናወናቸው ተጠቅሷል፡፡
በሮቦት የታገዘውን የቀዶ ህክምና ሂደት ከዩኒቨርሲቲው አንድ ማዕከል ላይ ሆነው ሲከታተሉ የነበሩት ፕሮፌሰር እሪስ፤ የሮቦት ማሽኑ ከዩኒቨርሲቲው አንድ የህክምና ምርምር ማዕከል ላይ ሆኖ ስራውን እንዲያከናውን መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ሪቻርድ ሀኔል ደግሞ ከአሜርካ ፊሎሪዳ ከ6 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆነው በሮቦት ማሽኑ እገዛ የተሳካ የስትሮክ ቀዶ ህክምና ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡
በሮቦት ማሽን የታገዘው የስትሮክ ቀዶ ህክምና በቀጣይም በተማሚዎች ላይ በደንብ ተግባራዊ ሲደረግ ለዘርፉ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የህክምና ቡድኑ በሰጠው ገለጸ ተመላክቷል፡፡
ባለፈው ወር ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማነቱ የተረጋገጠው በሮቦት ማሽን የታገዘው የስትሮክ ህክምና ሙከራ የሁለት ሀገራት የምርምር ቡድኖች የተሳተፉበት ሲሆን፤ ሮቦት ማሽኑን በማምረት ሴንታት የተባለ ኩባንያ እንዲሁ የአጋዥነት ሚናውን መወጣጡን ቢቢሲ ዘግቧል።
