“የፀጥታ ሃይሉ በመጠናከሩ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም”
በየዓመቱ በድምቀት በሚከበረውና የበርካታ ቱሪስቶች መስህብ በሆነው የአክሱም ጽዮን የንግስ ክብረ በዓል ላይ ዘንድሮም 2 ሚሊየን ገደማ ሰዎች ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገብረ መድኀን ፍፁምብርሃን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ጽ/ቤቱ ለበዓሉ ከሁለት ወራት በፊት ዝግጅት መጀመሩን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ክብረ በዓሉን የሚያስተባብሩ የተለያዩ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውንና የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዓሉን ለመታደም ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚመጡ ዜጎች ባሻገር በርካታ ቁጥር ያላቸዉ ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ተሳታፊዎች መኖራቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ በዚህም ህዳር 17 እና 18 ቀን 2018 ዓ.ም ከአማራ ክልል 12 አውቶብሶች እንግዶችን ይዞ እንደመጣና በተመሳሳይ ከሐረርና ድሬደዋ የሚመጡትን ተሳታፊዎችም በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ጽ/ቤቱ ለእንግዶቹ ማረፊያ ት/ቤቶችንና ሆቴሎችን ያዘጋጀ መሆኑን፣ በቀን ወደ ከተማዋ ይደረግ የነበረው በረራም ወደ 8 ከፍ መደረጉን በመጥቀስ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አመስግነዋል፡፡ ክፍያውንም በሚመለከት “አምና አስከፍቶን ነበር፤ ነገር ግን ዘንድሮ 20 በመቶ ቅናሽ አድርጓል ” ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ከበዓሉ ቀደም ብለዉ ባሉት ቀናት በርካታ ቁጥር ያለዉ ታዳሚ ዘንድሮ መመልከታቸዉን የገለጹት ኃላፊው፤ የሰላም ሁኔታውን በተመለከተ የፀጥታ ሃይሉ በመጠናከሩ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም ብለዋል፡፡
