በአማራ ክልል ደ/ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ፣ በአባይ ወንዝ ዳርቻ በሚገኘው የአባይ ገዳመ አስቄጤስ አቡነ አረጋዊና ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም በሐምሌ 15/2018 ዓ.ም በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሁለት መነኮሳት ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 14 መነኮሳት በተለያየ ደረጃ መጎዳታቸውን የገዳሙ አስተዳዳሪዎችና የወረዳው ቤተክህነት ኃላፊዎች ገለጹ።
የወረዳው ቤተክህነት ቃል፣ በገዳሙ ከነበሩት 16 መነኮሳት ውስጥ 14ቱ በጥቃቱ ተመትተዋል፤ ሁለቱ ብቻ ጉዳት አልደረሰባቸውም።
ከተጎዱት መካከል ሁለት መነኮሳት ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 11 በመካነሰላም ጠቅላላ ሆስፒታል ሕክምና ይገኛሉ። አንዲት መነኩሴ በከባድ ጉዳት ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ተዛውረዋል።
” ፍንዳታውን ሰምቼ ‘ወዮ’ እያልኩ ስሄድ መሬት ላይ ወድቀው አገኘኋቸው ! “
በወቅቱ በገዳሙ የነበሩት እማሆይ ወለተ ማርያም ለጀርመን ድምጽ ሬድዮ እንደተናገሩት፣ መነኮሳቱ የክረምት እህል ዝግጅት እያካሄዱ ባሉበት ወቅት ጥቃቱ ተፈጽሟል።
” ከዛ ስር እቤቱ አጠገብ የሆነ ዛፍ አለ አዚያ፤ ከዛ ስር ስብስብ ብለው እየለቀሙ ነበረ። እኔ አብሬ እለቅም ነበረ ተለይቼአቸው ሌላ ሥራ ለመሥራት ወደዛኛው ቤት ሄድኩኝ። ወዲያው ግን የሆነ ፍንዳታ ነገር በጣም መለየት ያቀተኝ ድምፅ ሰማሁኝ።
በቃ እንደመታቸው ስላወቅኩ ‘ወዮ’ እያልኩኝ ስሄድ ድፍት ድፍት ብለዋል አራቶች። ነካ ነካ ሳደጋቸው ምንም ራሳቸውን ስተዋል እናቶቹ ናቸው። እዛ ደም እየፈሰሳቸው የሚሯሯጡ የሚያለቅሱ ልጆች አሉ። እነሱን ጎተት አድርገን ወደጥግ ብለን እነሱን ደማቸውን ለማሰር እንዳይፈስ ለማድረግ ሞከርን…” ብለዋል።
የመካነ ሰላም ወረዳ ቤተክህነት ኃላፊዎችም፣ ጥቃቱ የተፈጸመው መነኮሳቱ ተሰባስበው እህል እያበጠሩ፣ እያዘጋጁና ሽንኩርት እየከተፉ በነበረበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።
” ሁለቱ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ 14 ሰዎች ተጎድተዋል! “
የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ኤልያስ ተሻገር ለጀርመን ድምጽ ሬድዮ ፤ ” አንዷ ወዲያውኑ እዚያው ላይ ሕይወቷ አለፈ፤ ሌላኛዋ ወደ መካነ ሰላም ሆስፒታል እየመጣን በመንገድ ላይ ሕይወቷ አለፈ። ጠቅላላ 14 ሰዎች ተጎድተዋል “ ሲሉ ተናግረዋል።
” ድሮኗ ስታስስ ቆይታ ነበር ! “
በአካባቢው የድሮን ጥቃቱ ከመከሰቱ በፊት የድሮን አሰሳ የነበረ መሆኑን የሚናገሩት አባ ወልደ ሚካኤል፤ ምናልባትም ከአካባቢው በቅርብ ርቀት የነበሩት ታጣቂዎችን ለመምታት ያለመ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።
” ድሮኗ እስከ ሦስት ሰአት እስከ አራት ሰዓት ስትዞር ቆይታ ወዲያዉ ድምጿን አጠፋችና አራት ሰዓት ላይ ላይ ያንን ክስተት ፈጠረች፤ ተጣለ ማለት ነዉ የመሣሪያውን። ቀን አራት ሰአት ላይ። ያው ምክንያቱ እነሱን የ ‘ ፋኖዎችን አገኘን ‘ ይሁን ወይም ምን ይሁን አልገባንም እኛ ዞሮ። ያው እንግዲህ ለነሱ የታሰበ ይሁን አላወቅንም እኛ። እዛ አካባቢ ይንቀሳቀሳሉ፤ የሚንቀሳቀሱትም ገዳሙ ውስጥ ሳይሆን ከገዳሙ ውጭ ነው። ኬላ አላቸው የራሳቸው፤ ከኬላው ነው የሚንቀሳቀሱት እነሱ። ያ ድሮንም ሲጣል እነሱ ኬላው ናቸው ያሉት ” ብለዋል።
በጥቃቱ የገዳሙ ተግባር ቤት፣ ለዓመታዊ ፍጆታ የተዘጋጀ እህል፣ የውኃ ታንከርና የውኃ መስመሮች መጎዳታቸውን እማሆይ ወለተ ማርያም ገልጸዋል።
መነኮሳቱ የሚጠቀሙበት ምጣስ ቤት (የእንጀራ መጋገሪያና የወጥ ማብሰያ ቦታ) በጥቃቱ መውደሙን ከወረዳው ቤተክህንነት ማረጋገጥ ችሏል።
” ‘ አምጡና ሕክምና አስገቦቸዉ ‘ ብለዉ ፤ አምጥተን ሕክምና አስገብተናል ! “
የቦረና ወረዳ ቤተ ክህነት ኃላፊ ሊቀ ካህናት ቀሲስ እንዳለ ሰማኝ ለጀርመን ድምጽ በሰጡት ቃል ፤ አደጋው ከተከሰተ በኋላ በወረዳዉ አስተዳደር የተሽከርካሪ ድጋፍ ቁስለኞችን ወደ ሆስፒታል መውሰድ ተችሏል ብለዋል።
” ከፍተኛ ጉዳት ሁለት የደረሰባቸው ነበሩ፤ አንዷ አስቸኳይ ስለሆነ ሪፈራል ሆስፒታል ደሴ ያው ሄደዋል። የወረዳው መንግስት እንግዲህ ያው ቁስለኞች ወደ ሆስፒታል እንዲመጡ ፈቃድ እንሰጣለን፤ ትራንስፖርት ጠይቃችሁ እናግዛችኋለን፤ አምጡና ሕክምና አስገቦቸዉ ብለዉ ፤ በዛ መሰረት አምጥተን ሕክምና አስገብተናል ” ብለዋል።
@tikvahethiopia
