የኢትዮ ቴሌኮም የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በገጠርና በከተማ ባከናወነው የኔትወርክ ማስፋፋት ስራ የደንበኞቹ ቁጥር 90 ነጥብ 1 ሚሊየን መድረሱን አስታውቀዋል። የደንበኞቹ ቁጥር ከባለፈው ዓመት ሲነጻጸር በ8 ነጥብ 3 በመቶ ማደጉን አንስተዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም በ2018 በጀት ዓመት 215 ነጥብ 82 ቢሊዮን ብር ገቢ በማግኘት ዓመታዊ ዕቅዱን 99 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካቱን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
የኩባንያው ይኸው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ33 ነጥብ 2 በመቶ የላቀ ዕድገት የተመዘገበበት ነው።
ለተመዘገበው ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ካበረከቱ የአገልግሎት ዓይነቶች መካከል ዋናዎቹ የዳታ እና ኢንተርኔት አገልግሎት 31 ነጥብ 1 በመቶ፣ የሞባይል ድምጽ አገልግሎት 23 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ ይዟል።
ማሕበራዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አንጻር፣ በትምሕርት፣ ጤና እና ሰብዓዊ ድጋፍ ዘርፎች ኢትዮ ቴሌኮም ከ492 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ በስነ ምሕዳሩ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራና የገቢ ዕድል ፈጥሯል።
