በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸው ተከሳሾች “በፍትሕ ስም የባርነት እና የጭቆና ቀንበርን ማስተናገድ የማንችልበት ደረጃ ደርሰናል” ሲሉ አቤቱታ አቀረቡ።
አቤቱታቸው ምላሽ ካላገኘ ጉዳያቸውን ለመከታተል ችሎት እንደማይቀርቡ አስታወቀዋል።
ተከሳሾቹ የጽሑፍ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጉዳያቸው ለሚታይበት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሕገ መንግሥት እና ሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነው።
ሆኖም በወቅቱ አቶ ክርስቲያን ታመው እንደነበረና ይህንኑ ለችሎት ተናግረው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ መጠየቃቸውንና ችሎቱም የመጨረሻውን ምስክር ለመስማት ለሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ገልጸዋል።
በወቅቱ ችሎቱ የተቀጠረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የሚገኙበት የክስ መዝገብ ላይ የዐቃቤ ሕግን ምስክር ለመስማት እንደነበረም ተናግረዋል።
አክለውም ተለዋጭ ቀጠሮው ከተሰጠ በኋላ አንደኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያለው የተከሳሾቹን አቤቱታ በጽሑፍ ለፍርድ ቤት ማቅረባቸውን አመልክተዋል።
ባቀረቡት አቤቱታ ተከሳሾቹ “ከህግ አግባብ ውጭ በእስራትና በመንግስታዊ እገታ ፍትሕ ተነፍገን ከቆየን ሁለት አመታትን አስቆጥረናል” ብለዋል።
“ከነገ ዛሬ የፍትሕ ሂደቱ ይሻሻል ይሆናል ብለን ብንጠብቅም ከጊዜ ጊዜ ሂደቱ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ በእኛ በተከሳሾች ላይ ሰፊ የመብት ጥሰትና በደል እየተፈጸመብን ይገኛል” ሲሉ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።
“ችሎቱ ሙሉ በሙሉ ለመንግስትና ለገዢው ፓርቲ ወግኗል” ያሉት ተከሳሾች፤ አክለውም “ያልተቋረጠ ጫናና ይሉኝታ ቢስ ውሳኔዎችን በተደጋጋሚ ፈጽሞብናል” ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ በፍርድ ቤቱ ተፈጸሙ ያሏቸውን አስር “ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔዎች” በዝርዝር በአቤቱታቸው ላይ አስፍረዋል።
በዚህም ክስ ከመመሥረቱ በፊት ለወራት በወታደራዊ ካምፕ መቆየታቸውን ያስታወሱት ተከሳሾቹ፤ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ፍርድ ቤቱ “አጋቾችን” በሕግ ተጠያቂ እንዲያደረግ እና “እገታን መዳኘት እንዲያቆም” ያቀረቡትን ጥያቄ “ቸል በማለት እገታን ሕጋዊ አድርጓል” ሲሉ ኮንነዋል።
እንዲሁም “ህገ-መንግሥቱ የፈቀደልንን በዋስትና የመከራከር መብታችንን ያለበቂ ምክንያት ሙሉ በሙሉ በመገደብ በተራዘመ እገታ በማቆየት የከሳሽን ጥቅም ብቻ አረጋግጧል” ሲሉ ተችተዋል።
በተጨማሪም ችሎቱ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲጣሩ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ኮሚሽኑ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ተከሳሾች ላይ “ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት” ስለመፈጸሙ ለችሎቱ ሪፖርት ማቅረቡን ያስታወሱት ተከሳሾቹ።
ይሁንና ፍርድ ቤቱ “የደረሰብንን እና በገለልተኛ አካል የተረጋገጠ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳላየ አልፎታል” ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች የተፈጸመብንን “የአጥንታችን ስብራት፣ የስጋችን መቁሰል፣ የአእምሯችን መድማትና የሞራል ጉዳት” በሪፖርቱ በግልጽ ቀርቦ እያለ ይልቁኑ ሪፖርቱ፤
“መንግስትን፣ የመንግስት የደህንነት ተቋማትንና ባለስልጣናትን የሚያስጠይቅ ሆኖ በመገኘቱ የተነሳ ገመናችንን ተመልክቶ በዝምታ ማለፉ ከበደል ፈጻሚዎቹ ያልተናነሰ ጥቃት እንደፈጸመብን እንቆጥረዋለን” ሲሉ አመልክተዋል።
ተከሳሾቹ “ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ትክክል አለመሆኑን አይቶ አሻሽሎ እንዲያቀርብ በይግባኝ የሰጠውን ብያኔ የስር ፍርድ ቤቱ ቀባብቶ አልፎታል” ሲሉ ከቀረበባቸው ክስ ጋር የተያያዘ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ “የተከሳሾች መብት በመተላለፍ” የክስ መዝገቡ ላይ የቀረቡ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች “ዝርዝር እና ማንነት እንዳይገለጽ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል የተከሳሾችን መብት አጣቧል” ሲሉ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን የተመለከተ አቤቱታ አቅርበዋል።
ምስክሮቹ “ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው” መሆናቸው በዐቃቤ ሕግ ቢገለጽም እስካሁን ችሎት ፊት የቀረቡት ምስክሮች “የመከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሆኑ እና ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው አለመሆናቸውን” እንደታዘቡ ተከሳሾቹ በአቤቱታቸው አመላክተዋል።
እንዲሁም በክስ መዝገቡ ላይ አቃቤ ህግ አቀርባቸዋለሁ ያላቸው ምስክሮች 21 መሆናቸውን ነገር ግን በምስክር ማሰማት ሂደት መጨረሻ ላይ አንድ ምስክር ተለዋጭ እንዲሆንልኝ ሲል መጠየቁን ያስታወሱት ተከሳሾቹ፤
በወቅቱ ሁሉም ምስክሮች በችሎት ፊት ቀርበው ቃላቸውን ፊት ለፊት የሰጡ ቢሆንም ተለዋጭ ተደርጎ የተጨመረው የአቃቤ ህግ ምስክር ግን ከመጋረጃው በስተጀርባ ማንነቱ ሳይታወቅ እንዲመሰክር ፍርድ ቤቱ “በተለመደው ወገንተኛነቱ” ሆኖ መወሰኑንና ይህም የተፈለገበት ምክንያት ራሱ አቃቤ ህግ ወይም የፍትሕ ተቋማት ሰዎች “ከሳሽ፣ መስካሪና ፈራጅ ሆነው ለመቅረብ እንዲያመቻቸው መሆኑ አያጠራጥርም” ብለዋል።
በተጨማሪም በእስር ላይ በሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ላይ በተለይም በአቶ ዮሐንስ ቧያለው እና በአቶ ክርስቲያን ታደለ ላይ ጥቃት ያደረሰ።
“ተሳዳቢ አክቲቪስት” ላይ ክስ ብናቀርብም፤ ፍርድቤቱ “በሥነ ሥርዓት ህጉ መሰረት ዳኝነት ሳይታይ ያለምንም ክርክር ግለሰቡን ከመልቀቁም በላይ ግለሰቡ አሁንም በተጠቂዎች ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት እንዲያደርስ የሚያበረታታ አድሏዊ ውሳኔ አሳልፏል” ሲሉ ወቅሰዋል።
እንዲሁም ከአማራ ክልል በተለይም ከባህር ዳር ተይዘው የመጡ ተከሳሾች በአከባቢያቸው ለመዳኘት ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ተከሳሾች፤ ሆኖም ፍርድ ቤቱ “የተከሳሾችን ችግር ከምንም ባለመቁጠር አግባብነት ያለው ምላሽ መስጠት አልቻለም” ብለዋል።
በዚህም “ፍርድ ቤቱ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት አለመቻሉን እንረዳለን” ያሉት ተከሳሾቹ፤ “በሂደትም የመሻሻል ጭላንጭል ቢኖር ዕድል ለመስጠት” እስከ አሁን የፍርድ ሂደቱን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ስለሆነም “በፍትሕ ስም የባርነት እና የጭቆና ቀንበርን ማስተናገድ የማንችልበት ደረጃ ላይ በመድረሳችን” እንዲሁም “ፍርድ ቤቶችና ዳኞች አጠቃላዩም የፍትሕ ስርዓት ተፈትነው የወደቁ መሆናቸውን በበቂ ሁኔታ በተግባር በማረጋገጣችን የጠቀስናቸው ችግሮች እስካልተቀረፉ ድረስ በዚህ ችሎት ቀርበን ለመዳኘት ዝግጁ አለመሆናችንን እንገልጻለን” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የችሎቱ ዳኞች አቤቱታውን ካነበቡ በኋላ “አቤቱታው ችሎት አንቀርብም የሚል ነው፤ ይሄንን አንቀበልም፤ በዳኞች ላይ ተቃውሞ ካላችሁ ዳኞች ይነሱልን ማለት ትችላላችሁ” ሲሉ መግለጻቸውን ጠበቃ ሰለሞን አብራርተዋል።
በምላሹ አቶ ዮሐንስ ቧያለው “አቤቱታችን፤ ያቀረብነውን ቅሬታ እንድትፈቱልን ነው። ችሎት አንቅርብም ያልነውም ቅሬታችን የማይፈታ ከሆነ ነው” ማለታቸውን አክለው ገልጸዋል።
አቶ ዮሃንስ ቧያሌው እና አቶ ክርስትያን ታደለን ጨምሮ 52 ግለሰቦች በአማራ ክልል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ውለው የሽብር ወንጀል ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወቃል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዮሃንስ ቧያሌው በሆኑበት በዚህ የክስ መዝገብ ሥር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ካሳ ተሻገር፣ አቶ እስክንድር ነጋ ፣ አቶ ዘመነ ካሴ እና ዶክተር ጫኔ ከበደ ይገኙበታል።
ለተከሳሾች እና ጠበቆቻቸው የደረሰው የክስ ዝርዝር ተከሳሾች “የፖለቲካ ርዕዮትን በኃይል ለማስፈፀም በማሰብ የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤትን ዓላማ ለማስፈፀም” ተሰባስበው መምራት የሚል ክስ ነው።
የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ክሱን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ግለሰቦቹ ክስ የተመሠረተባቸው “የፖለቲካ ርዕዮትን በኃይል ለማስፈጸም በማሰብ ከአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት ጋር በመደራጀት” ነው።
Addis standard
