የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ፣ የሊቀ ጳጳስነት ኃላፊነታቸውን በጡረታ ምክንያት ማስረከባቸው ተሰማ።
ብፁዕነታቸው ያቀረቡትን ከኃላፊነት የመነሳት ጥያቄ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዎ 14ኛ የተቀበሉት ሲሆን፣ ውሳኔው በቅድሥት መንበር ልዩ መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ አማካይነት ይፋ ሆኗል።
በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ምትክ የቀድሞው የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ አዲሱ፣ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሹመዋል። ቤተክርስቲያኗ ባወጣችው ይፋዊ መግለጫ፣ አዲሱ ተሿሚ የአገረ ስብከቱን መንፈሳዊ አገልግሎት በበላይነት እንደሚመሩ ታውቋል።
