የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ዘመኑ የሚጠይቀውን የተሻለ ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን በርካታ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል።
ከነዚኽም ሥራዎች መካካል የምርጫ ጣቢያዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ በመልከዓ ምድር የመረጃ ሥርዓት (ጂ.አይ. ኤስ) አማካኝነት መረጃቸውን በዘመናዊ መንገድ ማደራጀት ይጠቀሳል፡፡
ይኽንንም ተከትሎ ቦርዱ በሶማሌ ክልል የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችን በተገለጸው የመረጃ ሥርዓት የመመዝገብ ሂደትን አስመልክቶ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይቷል።
የውይይት መድረኩን የመክፈቻ ንግግር የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ያደረጉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም የምርጫ ጣቢያዎችን በመልከዓ ምድር የመረጃ ሥርዓት የማደራጀት ፋይዳው የምርጫ ጣቢያዎቹን መረጃ ወቅታዊ ለማድረግ ነዉ።
የምርጫ ጣቢያዎቹን ትክክለኛ መገኛ ለማወቅ፣ ጣቢያዎቹ በምርጫ ሕጉ ላይ በተደነገገው አግባብነት ባላቸውና ገለልተኛ ምርጫ ለማድረግ በሚያስችሉ ቦታዎች መቋቋማቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የቦርዱን ሰብሳቢ ንግግር ተከትሎ የቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ብሩክ ወንደወሰን የምርጫ ጣቢያዎችን በቴክኖሎጂ ታግዞ መረጃቸውን የማደራጀት ሂደት ምን ሊመስል እንደሚችልና ሥራው በታሰበው ጊዜ እንዲከወን ለማስቻል ከክልሉ መንግሥት ስለሚጠበቀው ኃላፊነት ገለጻ ሰጥተዋል።
ከተሣታፊዎቹ የተለያዩ ማብራሪያ የሚሹ አስተያየቶች የተነሡ ሲሆን፤ በቦርዱ ሰብሳቢና በቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል ኃላፊው አማካኝነት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
ቦርዱ ቀደም ሲል በአፋር፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በድሬዳዋ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ እና (በከፊል በሶማሊ እና በኦሮሚያ) ክልሎች ጣቢያዎቹን በተጠቀሰው የጂ.አይ. ኤስ ሥርዓት መመዝገብ ችሏል፡፡
