“ታሪክ ባይረሳም ሰው ይረሳል፤ ደግ ከሆነም ይቅር ማለት ይችላል!!”

Date:

የኢጣሊያዋ ጠቅላይ ሚ/ር ጆርጂያ ሜሎኒ በአፍሪካ በኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ምክንያት ለአፍሪካ የኢጣሊያ ፎረም/የጋራ መድረክ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሯ በወራት ልዩነት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይሄ ሁለተኛቸው ነው። ኢትዮጵያን ቤተኛቸው ለማድረግ የፈቀዱ ይመስላሉ። በርግጥ ኢጣልያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ የሆነች አገር ናት። ታላቁን የኅዳሴ ግድብ ለመገንባት በተጓዝንባቸው ትግዕሥትን የሚፈታተኑ ሂደቶች ሁሉ ኃያላኑ ሀገራት እና እንደ የዓለም ባንክና IMF የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የብድር ተቋማት ጀርባቸውን በሰጡን ጊዜ- ጣልያን በሳሊኒ ካምፓኒ በኩል የኅዳሴውን ግድብ ዕውን በማድረግ አጋርነታቸውን ያሳዩን ወዳጆቻችን ናቸው።

ቪቫ ኢትዮጵያ! ቪቫ ኢጣልያ! ቪቫ ጆርጂያ ሜሎኒ!!

ይህን የኢጣልያ ጠቅላይ ሚ/ር ጉብኝትና ሞቅ ደመቅ ያለ አቀባበል የታዘበ አንድ ወዳጄ እንዲህ አለኝ።

“… ለመሆኑ ይህቺ ሴት ፋሽስቱ ሞሶሎኒ በሕዝባችን ላይ ላደረሰው ጭፍጨፋ፤ አሰቃቂ ግፍና መከራ ይቅርታ ጠይቃለች፤ ስድስት ኪሎ/አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት በሚገኘው በሰማዕታት ሐውልት ተገኝታ በይቅርታ መንፈስ የአበባ ጉንጉን አኑራለች ወይ?!” ሲል ቁጭት በተጫነው ስሜት ጠየቀኝ።

ጥያቄው ተገቢ ነው!! ግን እንዲህም ሆኗል።

አገራችን ፋሽስት ኢጣልያ ከአገራችን ተሸንፎ የወጣበትን የድል/የዐርበኞች ቀን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓልን ባከበርንበት ወቅት በጊዜው የኢጣልያ ጠቅላይ ሚ/ር የነበሩት ሲልቪዮ በርሊስኮኒ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር።

በታሪክ ከ75 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢጣልያ ጠቅላይ ሚ/ር በአካል አዲስ አበባ በመገኘት በፋሽስት ኢጣልያ ለተጨፈጨፉ ወገኖቻችን መታሰቢያ በቆመበት የሰማዕታት ሐውልት ስር ጉንጉን አበባ በማስቀመጥ ታሪክ ሠርተዋል፤ በርሊስኮኒ ያን የፅልመት ታሪክ በይቅርታ መንፈስ አድሰዋል። ኢትዮጵያችንም ይህን የወዳጅነት መንፈስ ተቀብላለች!!

የማስታውሰው በወቅቱ የ75ኛ የድል/የዐርበኞች ዓመት በዓልን ለመዘከር በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UN/ECA) የመሰብሰቢያ አዳራሽ የታሪክ ዐውደ-ጥናት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህ መድረክ ላይ የሁለቱ አገራት (የኢትዮጵያና የኢጣልያ) ግንኙነት በኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት፤ በጥንታዊት ኢትዮጵያ ዐርበኞች ማኅበር ፕሬዚደንት በሆኑት በልጅ ዳንኤል መስፍን ጆቴ እንዲሁም በኢትዮጵያውያን አባትና በእናት ጀግኖች አርበኞች የተሰማው ድምፅ እንዲህ የሚል ነበር።

በፋሽስት ኢጣልያ መንግሥት የደረሰብንን ጭፍጨፋና ግፍ የሰው ልጅ ልርሳው ቢል እንኳ ታሪክ አይረሳውም፤ ያን የግፍ ታሪክ ለሰው ልጆች መማሪያ ይሆን ዘንድ ታሪክ መዝግቦታል፤ ኢጣልያና ኢትዮጵያ፤ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ግን በይቅርታ መንፈስ ወዳጅነታቸው፤ አጋርነታቸው እየታደሰ ቀጥሏል፤ ይቀጥላልም!!

ረጅም ዘመን ለኢትዮጵያና ለኢጣልያ ወዳጅነት፤ አጋርነት!!

ለወጌ መቋጫ፤ የኢጣልያን ጠቅላይ ሚ/ር ጆርጂያ ሜሎኒ የኢትዮጵያ ጉብኝት አንድ የታሪክ ግጥምጥሞሽን አስታወሰኝ።

ኢጣሊያዊቷ ዕውቅ ጋዜጠኛ የነበረችው፣ የዓለማችንን ታላላቅ ሰዎች ቃለ-መጠይቅ በማድረግና በድፍርቷ፣ በሞጋች ጥያቄዋ የምትታወቀው አርያና ፌላቺ በ1964 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ነበር። አመጣጧም “የአፍሪካ አባት፣ የዓለማችን ምርጥ ሰው/መሪ” በሚል የታይምስ መጽሔት ትልቅ ክብርን የቸራቸውን ግርማዊ፣ ቀዳማዊ ዐጤ ኃ/ሥላሴን ቃለ-መጠይቅ ለማድረግ ነበር።

በሰኔ 1964 ዓ.ም. ንጉሥ ኃ/ሥላሴ ሰማንያ ዓመታቸውን ሊይዙ ሲሉ የቃለ መጠይቆች ንግሥት የነበረችው ጣልያናዊቷ ኦሪያና ፋላቺ ወደ ቤተ መንግሥታቸው መጣች። ደፋሯ ጋዜጠኛ የምዕተ ዓመቱን ታላላቅ ሰዎች በራቸውን ለመከፋፈት የቻለች ናት። ፋላቺ ጥያቄዎቿን በቅድሚያ እንድታቀርብና ሱሪ እንድትለብስ ታዘዘች። የልብስ ምርጫቸውን ብትቀበልም ንጉሠ ነገሥቱ ጥያቄዎቿ ሙሉ በሙሉ እንዲደርሳቸው ግን አልፈቀደችም።

ጋዜጠኛ አርያና ፌላቺ ከዐጤ ኃ/ሥላሴ ጋር ያደረገችውን ቃለ-መጠይቅ፤ የሂብሪው ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ የታሪክና ፖለቲካ አንጋፋ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤርሊች፤ “The Rise and Fall of Haileselassie” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ አካተውታል። በጥቂቱ ላስታውሰው፤

ኦሪያና ፋላቺ፡- ጃንሆይ ጣልያንን በጎበኙ ጊዜ ጣልያኖች እርስዎ ላይ ጦርነት በማወጃጀቸው ከመንገዳቸው ወጥተው ይቅርታ ሲጠይቅዎ ነበር። በአንድ ቃልም በ1928 ዓ.ም. የተደረገው “የሙሶሊኒ ጦርነት” ነው ብለዋል። ይህ አላሳመነዎትም?

ንጉሥ ኃይለሥላሴ፡- በጣልያኖች እና በፋሺስቶች መካከል ልዩነት ነበር ማለት ለኛ የሚተው ነገር አይደለም። ይህ የእናንተ ኅሊና የሚወስነው ነው። አንድ ሀገር ማንኛውንም መንግሥት ተቀብሎ ካኖረ ያ ሀገር ለዚያ መንግሥት ዕውቅና ሰጥቶታል ማለት ነው።

እኛ ግን መናገር ያለብን የሙሶሊኒን ጦርነት ከሙሶሊኒ መንግሥት ሁሌም ለይተን እናይ እንደነበረ ነው። ሁለት የተለያዩ ነገሮች ነበሩ። የኢትዮጵያን ወረራ በተመለከተ የሙሶሊኒን መንግሥት መገመት ያቅተናል። ለሕዝቡ የሚበጀውን የሚያውቅ መንግሥት ነው፤ የሙሶሊኒ መንግሥት እኛን ሲወር የጣልያንን ሕዝብ እንደሚጠቅም አምኖ መሆኑ ግልጽ ነው።

ኦሪያና ፋላቺ፡- ጃን ሆይ ያሉት አልገባኝም ይሆናል። ሙሶሊኒን ዛሬ እንዴት እንደሚያዩት መጠየቅ እችላለሁ?

ንጉሥ ኃይለሥላሴ፡- እሱን ከመገመት እንታቀባለን። ሞቷል፤ የሞተ ሰው ላይ ዳኝነት ማሳለፍ ምን ጥቅም አለው? ሞት ሁሉንም ነገር ይቀይራል፣ ሁሉንም ጠራርጎ ይወስዳል። ስሕተቶችንም ጭምር። ለእኛ መልስ መስጠት በማይችል ሰው ላይ ጥላቻ ወይንም ቁጣ መናገር አንወድም። ይህ ሀገራችንን ለወረሩት ለሌሎቹም ይሠራል። ግራዚያኒ፣ ባዶግሊዮ። ሁሉም ሞተዋል። ዝምታ ይሻላል።

ሙሶሊኒን ያገኘነው በ1916 ዓ.ም. ንጉሠ ነገሥት ከመሆናችን በፊት ጣልያንን በጎበኘንበት ወቅት ነው። እንደ እውነተኛ ጓደኛም ሞቅ ባለ አቀባበል ተቀብሎናል። ደግ ነበር። ወደነውም ነበር። ስለጥንቱ እና ስለወደፊቱ በግልጽ ተነጋግረናል። እንድናምነውም አነሳስቶን ነበር። ከውይይቱ በኋላም የነበሩን መጥፎ እይታዎች ጠፉ። ኋላ ግን ቃሉን አጠፈ። መቼም ያልተረዳነውና ገብቶን የማያውቀው ይሄ ነው። አሁን ግን አስፈላጊ አይደለም።

ኦሪያና ፋላቺ፡- እንደዛ ከሆነ ጃንሆይ እነዛን ዓመታት እንዴት ነው አሁን የሚያዩአቸው? በእርስዎ/በሀገርዎ ላይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት?

ንጉሥ ኃይለሥላሴ፡- … ጣልያኖቹ በእኛ ላይ ያደረጉትን መርሳት አንችልም። በእናንተ ምክንያት ብዙ ተሰቃይተናል። በሌላ በኩል ግን ምን ማለት እንችላለን? ፍትሐዊ ያልሆነ ጦርነት ቀስቅሶ ማሸነፍ ማንም ላይ ሊደርስ ይችላል።

በ1933 ዓ.ም. ወደ ሀገራችን እንደተመለስን ከጣልያኖች ጋር ወዳጆች መሆን እንዳለብን አወጅን። ዛሬ እውነትም ወዳጆች ነን። እናም. . . እንዲህ እንበል፤

ታሪክ ባይረሳም ሰው ይረሳል። ደግም ከሆነ ይቅር ማለት ይችላል። እኛም ደግ ለመሆን እንሞክራለን። አዎ ይቅር ብለናል። ግን አልረሳንም። አልረሳንም። ሁሉንም፣ ሁሉንም ነገር እናስታውሳለን።

ረጅም ዕድሜ ለኢትዮጵያና ኢጣልያ ወዳጅነት!!

ቪቫ ኢትዮጵያ! ቪቫ አፍሪካ! ቪቫ ኢጣልያ!

© በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተፈናቀሉ ዜጎች በተጠለሉበት አካባቢ በቋሚነት መኖር የሚያስችላቸው 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ከበኦሞ...

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...