በጥር ወር 2018 ዓ.ም የሀገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት መጠን 9.8 በመቶ መድረሱ ተገለጸ። ይህም ከአንድ ወር በፊት በታህሳስ 2018 ዓ.ም ከነበረው 9.7 በመቶ ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ ጭማሪ አሳይቷል።
ይሁን እንጂ የዘንድሮው የጥር ወር የዋጋ ግሽበት መጠን በጥር 2017 ዓ.ም ከነበረው 15.5 በመቶ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ቅናሽ የታየበት መሆኑ ተመልክቷል።
ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር የምግብና አልኮል ያልሆኑ መጠጦች ዋጋ በ10.4 በመቶ ማደግ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህም በዋናነት የአትክልት፣ የስጋ፣ የወተት ተዋፅኦዎች፣ የእንቁላል፣ የፍራፍሬ፣ የዘይትና የስኳር የመሳሰሉት የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በመጨመራቸው ነው።
በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት 9.0 በመቶ የደረሰ ሲሆን ትራንስፖርት (17.1 በመቶ)፣ ሌሎች እቃዎችና አገልግሎቶች (19.4 በመቶ)፣ ምግብ ቤቶችና ሆቴሎች (12.5 በመቶ)፣ የቤት እቃዎች (11.8 በመቶ) እንዲሁም የአልኮል መጠጦችና ትምባሆ እና ኮሙዩኒኬሽን እያንዳንዳቸው በ10 በመቶ ጭማሪ ተመዝግቦባቸዋል።
