ማዕከሉ በጅማ ዩኒቨርስቲ የህክምና ማዕከል ሆስፒታል መከፈቱ ተነግሯል፡፡
“Palliative care” ወይንም እንክብካቤ እየሰጡ ማስታገስ የሚሰጣቸው ሰዎች የካንሰር ህሙማን ፣ ለረጅም ጊዜ በኦክስጅን ላይ የቆዩ እና ሌላም ሌላም ህመም ያለባቸው ናቸው፡፡
ይህ ዓይነቱ የህክምና አገልግሎት ገና እንደ ሀገር አልተለመደም ያሉን በሙያቸው የህፃናት እስፔሻሊስት እና የጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማእከል ዋና ክሊኒካ ዳይሬክተር ዶ/ር ሁንዴ አህመድ ናቸው፡፡
ከዚህ ቀደም ይህን አገልግሎት የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት ለህሙማን ይሰጧቸው እንደነበር እና አንዳንዶች ህመሞች በየቀኑ የጤና ባለሙያን ክትትል የሚፈልጉ በመሆናቸው ማዕከሉ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ህሙማኑ በየእምነታቸው እንዲጽናኑ እዛው የጤና ተቋም ውስጥ የጸሎትና ሌሎች አገልግሎቶች እየተሰጣቸው መቆየት እስከሚችሉበት ድረስ እንደሚረዱ ነግረውናል፡፡
ህሙማን ከሚያስፈልጋቸው የህክምና አገልግሎት አንዱ ኦክስጅን እንደሆነ ዋና የክሊኒካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሁንዴ አህመድ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ኦክስጅን ከአዲስ አበባ በማስመጣት አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
አሁን ላይ ሆስፒታሉ በራሱ ኦክስጅኖቹን መሙላት እንደጀመረና ከአንድ ወር በኋላ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚችልም ሰምተናል፡፡
ሸገር 102.1
