የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ውስጥ የሚኖር የሥርዓት ለውጥ “ሊከሰት የሚችል ምርጥ ነገር” ነው በማለት በአገሪቱ የአገዛዝ ለውጥ ላይ ያላቸውን ድጋፍ ገለፁ።
“ለ47 ዓመታት ሲያወሩ፣ ሲያወሩና ሲያወሩ ቆይተዋል። እስከዚያው ድረስ ግን ብዙ ሕይወት አጥተናል” ሲሉ አርብ ዕለት ተናግረዋል።
ትራምፕ ኢራንን ማን እንዲያሰተዳድራት እንደሚፈልጉ ለመግለጽ ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ ሥልጣን ሊረከቡ የሚችሉ “ሰዎች አሉ” ብለዋል። የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ለትራምፕ የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች እስካሁን ድረስ ምላሽ አልሰጡም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ኢራን የኒውክሌር ስምምነት እንድታደርግ ጫና ለማሳደር ሁለተኛ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ልካለች።
በዓለም ላይ ትልቁ እና አዲሱ የአሜሪካ የአውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ የሆነው ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ “በቅርቡ” ከካሪቢያን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመንቀሳቀስ ተዘጋጅቷል ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘውን ሁለተኛውን የአሜሪካ የጦር መርከብ ለመቀላቀል የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቡ ሲንቀሳቀስ የሚያሳይ ምስል አጋርተዋል።
ፔንታጎን የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቡን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የላከው በጥር ወር ነበር።
ይህ የሆነው ዩናይትድ ስቴትስ የኢራን መንግሥት በሺዎች የሚቆጠሩ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ላይ የሚፈጽመውን ግድያ ለማስቆም አገሪቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ካስፈራራች በኋላ ነው።
ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የኒውክሌር ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ በኢራን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ቢዝቱም፣ ረቡዕ ዕለት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በዋይት ሐውስ ከተወያዩ በኋላ ከቴህራን ጋር የሚያደርጉት ውይይት እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
BBC Amharic
