ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ኒውክሌርን የተመለከተ ውይይት እንደሚቀጥል ለጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መግለጻቸውን አስታወቁ።
ኢራን ስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ ግን እርምጃ እንደሚወሰድ ትራምፕ አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ እና ኔታንያሁ ትናንት በዋይት ሀውስ ሲገናኙ ውጥረት ስለሰፈነበት መካከለኛው ምሥራቅ ተወያይተዋል። የኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መርሃ ግብርም ከውይይት አጀንዳዎቻቸው አንዱ ነበር።
ትራምፕ፤ ኢራን ዩራንየም ማበልጸግ እንድታቆም፣ የባለስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራሟን እንድታጥፍ እንዲሁም እንደ ሐማስ እና ሔዝቦላህ ያሉ ታጣቂዎችን እንዳትደግፍ ጫና እንዲያሳድሩ ኔታንያሁ እንደሚፈልጉ ተገልጿል።
ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመገደብ ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች። በምላሹም የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱ ጠይቃለች።
ኢራን ሌሎች የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን እንደማትቀበል ገልጻለች።
ትራምፕ እና ኔታንያሁ ከመገናኘታቸው አስቀድሞ፤ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን አገራቸው ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ሁለተኛ ዙር ድርድር “ከልክ ያለፈ ጥያቄ አትቀበልም” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ በኩል የሚቀርቡ ቅድመ ሁኔታዎችንም ተችተዋል።
ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ኔታንያሁ በዋሽንግተን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ የአሁኑ ስድስተኛቸው ነው። ይህም የየትኛውም አገር መሪ ወደ አሜሪካ ካደረገው የጉዞ ብዛትይበልጣል።
መሪዎቹ ለሦስት ሰዓት ገደማ ከተወያዩ በኋላ ትራምፕ ጋዜጣዊ መግለጫ አልሰጡም። በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ውይይቱ “በጣም ጥሩ ነበር” ብለዋል።
“ምንም ውሳኔ ላይ አልደረስንም። ከኢራን ጋር ድርድር መቀጠል አለበት የሚለውን አጽንዞት ሰጥቼ ተናግሬያለሁ” ሲሉም አክለዋል።
BBC amharic
