ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴና ዝውውር ላይ የተጣሉ አብዛኛዎቹን ገደቦች አንስቷል። ገንቢ እርምጃ ነው። ነገር ግን፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ስር የሰደደውን የመንግስት ሚና በልኩ በመገደብ ኢኮኖሚውን ከመንግስት ቁጥጥርና ጣልቃ ገብነት ነጻ ከማድረግ አኳያ ብዙ ይቀረናል።
የውጭ ምንዛሪ ይሁን የሀገር ውስጥ የመገበያያ ገንዘብ ብሔር፣ ሐይማኖት፣ ዘር ወይም ድንበር ስለሌለው በነጻ መንቀሳቀስ በተፈቀደለት ሀገር ውስጥ በነጻ ገበያ ውድድር ስርዓት በመመራት ሰርቶ ያሰራል። እድገትንና ልማትን ያረጋግጣል።
እንቅስቃሴና ዝውውሩ ላይ ገደብ በሚጣልበት ሀገር ውስጥ ገንዘብ ብሔር ሃይማኖት ድንበር ስለማይገድበው መልኩን፣ ቅርጽና ይዘቱን እየለዋወጠና እየተሹለከለከ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለጥቁር ገበያ፣ ለደላላ፣ ለሙሰኞችና ለኮንትራባንድ አሳልፎ በመስጠት የሕገ ወጦች መጫወቻ ያደርገዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው በነጻ ገበያ ውድድር ላይ በተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴ ካልታገዘ በጥቁር ገበያና በሕጋዊ ምንዛሪው መካከል ያለውን ልዮነት ማጥበብ ዘበት እንደሆነ ብዙዎቻችን ደጋግመን አሳስበናል። ጊዜ ቢፈጅም ከዛሬ ጀምሮ የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴ በአንጻራዊነት ነጻ የመሆኑ ውሳኔ ሊመሰገን የሚገባው ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
አሁንም ግን ገና ገና ብዙ ይቀረናል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በነጻ ገበያ ውድድር ስርዓት የሚመራና ከመንግስት ተጽእኖ የተላቀቀ እስኪሆን ድረስ ጥረታችን መቀጠል አለበት።
