የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው የ2024 የሰብአዊ መብት ሪፖርት ላይ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በፖለቲካዊ ጭብጥ የተሞሉ ስራዎቻቸውን ለማቅረብ ሲሞክሩ እንደታገዱና ለከፋ እንግልት እንደተዳረጉ አመለከተ።
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው፣ አንዳንድ አርቲስቶች በመንግስት ላይ ትችት በማቅረባቸው በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ እንደተመሰረተባቸውም ተገልጿል።
ዛሬ ይፋ የተደረገዉ ይህ ሪፖርት እንዳመለከተው ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰቱ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መካከል የፍርድ ውጪ ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እስሮች እና መሰረታዊ የዜጎች ነጻነቶች ላይ የተጣሉ ገደቦችን በዝርዝር አስቀምጧል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት (OHCHR) የተሰጠውን መረጃ በመጥቀስ፣ ከጥር 2023 እስከ ጃንዋሪ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ በመንግስት ሃይሎች፣ በኤርትራ ወታደሮች፣ በተቃዋሚ ታጣቂዎች እና ባልታወቁ አካላት በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ 1,351 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ሪፖርቱ አትቷል።
በተጨማሪም በመንግስት ሃይሎች ድሮን አማካኝነት በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ብቻ በ2023 አጋማሽ እና መጨረሻ ላይ 248 ሲቪሎች መሞታቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል።
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ባሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መረጃ፣ በመራዊ ከተማ በመንግስት ወታደሮች ከ50 በላይ ንጹሃን ዜጎች መሰብሰብ እና መገደላቸውም ተጠቅሷል።
የኦሮሞ ነጻነት ጦር (ኦነግ ሸኔ) እና የአማራ ፋኖ ተብለው የሚጠሩት ታጣቂዎችም ሰላማዊ ዜጎችን እና የመንግስት ባለስልጣናትን ህይወት ማጥፋታቸው በሪፖርቱ ተገልጿል።
ሪፖርቱ በመንግስት ሃይሎች በመገናኛ ብዙኃን እና በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ላይ የሚደረሰውን ጫናና እስር ጎላ አድርጎ አሳይቷል። የዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ነጻነት መቀነሱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መንግስትን በመተቸት ብቻ ለእስር እና ለእንግልት እንደተዳረጉ ሪፖርቱ አመልክቷል።
ሪፖርቱ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በተባሉ ባለስልጣናት ላይ የወሰደው እርምጃ “ውስን” እና “ግልጽ አይደለም” ሲልም ተችቷል።
CapitalNews
