በኦሮሚያ ክልል በሕገ-ወጥ ንግድ ወይም በኮንትሮባንድ ሲንቀሳቀስ የነበር ነዳጅ እና ቡና በቁጥጥር ሥር መዋሉን የክልሉ ንግድ ቢሮ ገልጿል።
የቢሮው ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር የሆኑት ጌታቸው ቆጲሳ እንደገለጹት፤ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ በክልሉ በተደረገው ክትትል በሕገ-ወጥ ንግድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከ8 ሺሕ 500 ሊትር ነዳጅ እና 31 ቶን የሚሆን ቡና በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ዳይሬክተሩ አክለውም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ በክልሉ በሕገ-ወጥ ንግድ የተያዙ ምርቶች አጠቃላይ ግምታቸው ከ88 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልጸው፤ ወደ 41 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።
“በዚህም መሠረት የሕገ-ወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል ንብረቱም በመንግሥት ተወርሷል” ሲሉ ገልጸዋል።
እንዲሁም፤ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ በክልሉ በተደረገው ክትትል የንግድ ፍቃድ ሳይኖራቸው ሲነግዱ በመገኘታቸው 2 ሺሕ 500 የሚሆኑ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ አድርገው ሲሸጡ የተገኙ 1 ሺሕ 646 የሚሆኑት የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ 286 የሚሆኑት የንግድ ፍቃዳቸው መታገዱንና የፁሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መኖራቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው በአንድ ወር ውስጥ ከ37 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ ቁጥጥር እና ክትትል ለማድረግ አቅዶ፤ ከ32 ሺሕ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ ክትትል ማደረጉን ጨምረው ገልጸዋል።
“በዘርፉ ያሉ መሠል ወንጀሎችን እና ሕገ-ወጥነትን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ የተቻለው ሕብረተሰቡን ጨምሮ ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ነው” ሲሉ አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል።
በአንድ አንድ አካባቢዎች በየጊዜው ቦታ በመቀያየር የሚነግዱ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር በዘርፉ ላይ ተግዳሮት መሆኑን የቢሮው ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር ተናግረዋል።
ቢሮው ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የቅንጅት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ጌታቸው ቆጲሳ አስረድተዋል።
ሕብረተሰቡ በምርቶች ላይ ባዕድ ነገር እየቀላቀሉ በሚሸጡ እንዲሁም ያለአግባብ የዋጋ ጭማሬ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር ለማድረግ ጥቆማቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
