አፍሪካ በ2030 ለሁሉም ዜጎቿ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ በየዓመቱ ከ25 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ተዘግቧል ። ይህ መጠን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከሚያስፈልገው ተጨማሪ 200 ቢሊዮን ዶላር ጋር ተደምሮ የአህጉሪቱን የፋይናንስ ጫና እጅግ ከፍ ያደርገዋል።
በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ፋይናንስ አወቃቀር ለዕርዳታ ሳይሆን ለብድር ቅድሚያ መስጠቱ ለአፍሪካ አገሮች አዲስ የዕዳ ጫና እየፈጠረ ነው። ይህ ሁኔታ አህጉሪቱ ቀደም ሲል ከነበረባት ከባድ የዕዳ ሸክም በተጨማሪ ተጨማሪ ብድር እንድትወስድ ይገፋፋታል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ይህ አካሄድ አፍሪካን ወደ ጥልቅ የጥገኝነት ወጥመድ ሊያስገባት ይችላል።
የተባበሩት መንግስታት ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሀብቶች ተቋም (UNU-INRA) ያወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ ብዙ ልቀት የሚያመነጩ ሀገሮች ፍትሃዊ የሆነ ድርሻቸውን ሳይወጡ፣ አፍሪካ ብቻዋን የሌሎችን የአየር ንብረት ምኞት ለማሳካት እየተገደደች፣ ወደ የከፋ የኃይል ድህነት ልትገባ እንደምትችል አመልክቷል።
አፍሪካ ለዓለም አቀፍ ልቀት አስተዋጽኦ ያደረገችው እምብዛም ባይሆንም፣ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረባት ነው። የአየር ንብረት ለውጡ በከተሞች ላይ ጉዳት ከማድረሱም በላይ የምግብ ዋስትና እጥረትን እያባባሰ መሆኑንም ተጠቁሟል።
CapitalNews
