ኢትዮጵያ በተለይም በርካታ ኢንቨስተሮችን መሳብ የሚችል አቅም ያላት በመሆኑ አፍሪካን ማዳረስ የሚችል ምርት ማምረት እንደምትችል የገለፁት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ ናቸው ፡፡
ይህንን ተከትሎም በሀገር ውስጥ ስትራቴጂ ውስጥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የመድኃኒት ማምረቻ ማዕከል መሆን ትችላለች የሚል ሀገራዊ እቅድ ተይዞ እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህ እቅድ ውስጥ ያለውን የፖሊሲ ምቹነትና ሀገራዊ ሁኔታዎች መነሻ በማድረግ በርካታ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እድል እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው ምርት ጥራቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ ከመሆኑ በላይ በዚህ ቁጥጥር ያለፈን መድኃኒት የትኛውም ሀገር ላይ ለመላክ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ሚኒስትር ዲኤታዋ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነትን መፈረሟን በማንሳት ይህም በቀላሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረቱ ምርቶችን ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለመላክ እንደሚያስችል ገልፀዋል።
በመሆኑም እነዚህና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ኢትዮጵያን የአፍሪካ የመድኃኒት ማምረቻ ማዕከል ሊያደርጓት የሚችሉ ጉዳዮች መሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትር ዲኤታዋ በዛ መሰረትም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
