የአለም አቀፍ የፍትህ ፕሮጀክት (WJP) ባወጣው የ2025 የሕግ የበላይነት መረጃ ጠቋሚ መሠረት ኢትዮጵያ ከ143 አገሮች መካከል 132ኛ ደረጃን ይዛለች። በዚህም በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት ከዓመት ዓመት ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል ብሏል።
ሪፖርቱ የሀገሪቱ ውጤት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ2.4 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሶ፤ ይህም ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ተቋማት እየደከሙ፣ የሲቪክ ምህዳሩ እየጠበበ እና የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ሲል ገልጿል።
እንደ የአለም አቀፍ የፍትህ ፕሮጀክት መረጃ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕግ የበላይነት ማሽቆልቆል በ2025 ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 68 በመቶ የሚሆኑ አገራት ማሽቆልቆል አሳይተዋል።
የአምባገነንነት ዝንባሌዎች መስፋፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የህግ የበላይነት መዳከም ዋነኛ ምክንያት ነው ያለው ተቋሙ፤ ይህም በመላው ዓለም ቁጥጥርና ሚዛናዊነት መዳከሙን እና የዳኝነት ነፃነት መሸርሸሩን አመላካች መሆኑን ገልጿል።
በአሁኑ ውቅት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ 34 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ 30ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ያለው የአለም አቀፉ የፍትህ ፕሮጀክት፤ ሩዋንዳ [በዓለም አቀፍ ደረጃ 39ኛ] በመሆን የተሻለ አፈጻጸም አላት ብሏል፤ በተጨማሪም ናሚቢያ እና ሞሪሽየስም በቀጠናው የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው አገራት መካከል ተካተዋል።
የኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ለተከታታይ ዓመታት እያሽቆለቆለ ይገኛል። ለአብነትም ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳውያኑ 2022 ከ140 አገራት ውስጥ 123ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ በተለይም “በሥርዓትና ፀጥታ ላይ መዳከም መታየቱ” ተገልጿል።
እንዲሁም በ2023 (እ.ኤ.አ) ከ142 አገሮች ወደ 129ኛ ደረጃ ዝቅ ያለች ሲሆን፤ በ2024 ደግሞ ደረጃዋ ከ142 አገሮች 130ኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ አገሪቱ በዚሁ ዓመት ወደ 132ኛ ደረጃ ዝቅ ብላላች።
በቀጠናው ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት መካከል ስትመደብ በ2022 27ኛ ደረጃ፣ ከ2023 እስከ 2025 ባሉት ጊዜያት ደግሞ 30ኛ ደረጃ ላይ ቆይታለች።
የ2025 የሕግ የበላይነት መረጃ ጠቋሚ፣ በመንግሥታዊ የሥልጣን ገደብ፣ ግልጽ በሆነ አስተዳደር እና መሠረታዊ መብቶች መከበር ላይ ከፍተኛ ማሽቆልቆሎች መኖሩን አመላክቷል። ኢትዮጵያ በእነዚህ በሦስቱ ቁልፍ መለኪያዎች ከዓለም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በ2025 “ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ፣ በመሰብሰብ ነፃነት እና በሲቪክ ተሳትፎ ያስመዘገበችው ውጤት የከፋ መሆኑን” የገለፀው ተቋሙ፤ ይህም ተመሳሳይ ማሽቆልቆል ካሳዩ ከ70 በመቶ በላይ ከሚሆኑ አገራት ዓለም አቀፍ አዝማሚያ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ጠቁሟል።
ሪፖርቱ፣ “የሲቪክ ምህዳር በዓለም ዙሪያ መጥበብ መባባሱን” በመግለጽ፣ “ይህም ሕዝባዊ ውይይትን እና የተጠያቂነት ዘዴዎችን አደጋ ላይ ይጥላል” ሲል አስጠንቅቋል። የአለም አቀፉ የፍትህ ፕሮጀክት አክሎም፣ የዳኝነት ነፃነት “ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ61–67በመቶ በሚሆኑ አገሮች” ውስጥ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት መሸርሸሩን ገልጿል።
በ2025 ኢትዮጵያ በመንግሥት ሥልጣን ገደብ 134ኛ ደረጃ፣ በመሠረታዊ መብቶች 138ኛ ደረጃ፣ በግልጽ የመንግስት አስተዳደር 135ኛ ደረጃ እና በሕግ ማስፈጸም 137ኛ ደረጃን ማስመዝገቧ እና ይህን ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ ሆነው የሚመደቡ ናቸው ተብሏል።
ሀገሪቱ በሙስናን በማስቀረት 96ኛ እና የወንጀል ፍትሕ በማስረጽ 101ኛ ደረጃ ላይ በመጀኘት ተወሰነ መሻሻል ቢኖርም በሌሎች መለኪያዎች ከዓለም አቀፉ አማካኝ በታች ትገኛለች ተብሏል።
የአለም አቀፉ የፍትህ ፕሮጀክት ሪፖርት ከመውጣቱ ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሚያዚያ 2017 ዓ.ም እስከ መስከረም ወር 2018 ዓ.ም ድረስ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልሎች ባደረገው ክትትልና ምርመራ የሰዎች የመንቀሳቀስ መብት በስፋት መጣሱን የሚያሳይ ሪፖርት አውጥቶ ነበር።
የአለም አቀፉ የፍትህ ፕሮጀክት (WJP) ዛሬ ባወጣው የ2025 የሕግ የበላይነት መረጃ ጠቋሚ መሠረት አምስቱ ከፍተኛ ደረጃ ያገኙ አገሮች ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን እና ኒው ዚላንድ ሆነዋል፤ በሌላ በኩል ቬንዙዌላ፣ አፍጋኒስታን፣ ካምቦዲያ፣ ሃይቲ እና ኒካራጓ ደግሞ ዝቅተኛውን ደረጃ ይዘዋል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ኤልዛቤት አንደርሰን፣ “የሕግ የበላይነት ለሰላም፣ ለፍትሕ እና ለብልጽግና መሠረት ነው፤ ሆኖም በብዙ የዓለም ክፍሎች መዳከሙን ቀጥሏል” ብለዋል። አክለውም “ይህን ሁኔታ ለመቀልበስ የሲቪክ ምህዳርን ለመጠበቅ፣ የዳኝነት ነፃነትን ለማጠናከር እና የመንግሥትን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ አስቸኳይ እርምጃ ያስፈልጋል” ብለዋል።
የዘንድሮው ጥናት የዓለምን 95 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ ከሚወክሉ ከ143 አገሮች የተሰበሰበ ሲሆን፣ ከ215,000 በላይ አባወራዎች እና 4,100 የባለሙያዎች ጥናቶችን መሠረት ያደረገ ነው።
ኢትዮጵያ “በህገ የበላይነት ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው 16 አገሮች መካከል 13ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ” ሲሆን፤ ይህም በስምንቱም የሕግ የበላይነት መለኪያዎች ላይ “ከፍተኛ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ችግሮች መኖራቸውን አመላካች መሆኑ” ተጠቁሟል።አስ
